ቀጥታ፡

ሕዝቡ ከጤና ሙያተኞች ጎን እንዲቆም የብልፅግና ፓርቲ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚችለው ሁሉ ከጤና ሙያተኞች ጎን እንዲቆም የብልጽግና ፓርቲ ጥሪ አቅርቧል።

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ሕክምና ማዕከል የሚያገለግል ሙሉ አልባሳት ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስረክቧል።

ፓርቲው ያደረገው ድጋፍ ስምንት ሺህ ጥንድ የእጅ ጓንትና 500 የሓኪሞች ኮቪድ-19 መከላከያ ልብስ (ቦዲ ሱት) ነው።

በድጋፍ መርሃ ግብሩ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ''ሕዝቡ ከጤና ሙያተኞች ጎን ይቁም'' ብለዋል።

የጤና ባለሙያ በቫይረሱ የተጠቁ ወገኖችን ለማከምና ሕይወታቸውን ለማትረፍ እያደረጉት ያለው ርብርብ ታሪክ የማይረሳው እንደሆነ ጠቁመዋል።

''ትልቅ መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ ሙያተኞቻችን ያለን ክብር እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው'' ሲሉ አቶ ብናልፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል ።


አቶ ብናልፍ ሕዝቡ በሚችለው አቅም ሁሉ ከጤና ሙያተኞች ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

''ሙያተኞች መበረታታትና መደገፍ አለባቸው፣ መላው ሕዝብ ከሙያተኞቹ ጎን መሆን አለበት'' ነው ያሉት።

ፓርቲው ያደረገው ድጋፍም ለሙያተኞቹ ያለውን ክብርና አድናቆት ለማሳየት መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ብናልፍ አክለውም ''የብልፅግና ፓርቲ ወረርሽኙ ወደ አገር ከመጣ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል'' ብለዋል።

በዚህም ለሕዝቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ሥራ ጀምሮ አቅም ለሌላቸው እንዲውል 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ የአገሪቷ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ መሥራቱን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው ድጋፉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለፓርቲው ምሥጋናቸውን ቸረዋል።

ቫይረሱን በመቆጣጠርና በመከላከል ረገድ በለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት እጅግ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር ዮሐንስ አያይዘውም ''ድጋፉ የጤና ባለሙያው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደረገውን ጥረት ያግዛል'' ብለዋል።

የቢሮው ኃላፊ የበሽታው ሥርጭት እየጨመረ ከመምጣቱ አንጻር የጤና ሙያተኛው ከሚሰራው ሥራ በላይ ሕዝቡ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም