ቀጥታ፡

ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የተከሏቸውን ችግኞች እንዲንከባከቡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13/2013 (ኢዜአ) የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የተከሏቸውን ችግኞች እንዲንከባከቡ ጥሪ አቀረበ።

በዘንድሮው ክረምት በመላ ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ዕቅድ ተይዞ እስካሁንም በመከናወን ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዘንድሮውን የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር በሐዋሳ ጀምረው በባሕርዳር አሳርገዋል።

የዘንድሮው የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር በእጅጉ የተሳካ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላው ስኬታማ ቢሆንም በእንክብካቤ አድገው የአረንጓደ ልማቱ ግብ እንዲሳካ ከወዲሁ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ  የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አሳስቧል።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በተቋማትም ይሁን በግለሰቦች የተተከሉ ችግኞች ሁሉ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

መትከል ብቻውን የአረንጓዴ ልማት ግብ ባለመሆኑ ጸድቀው እንዲያድጉ ለማስቻል ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ችግኞችን እንዲንከባከብ ጥሪ አቅርበዋል።

ችግኞች የተተከሉባቸው አካባቢዎች ከእንስሳት ንክኪ ነፃ እንዲሆኑ መጠበቅ ያስፈልጋልም ብለዋል።

የዓለም ሥጋት እየሆነ የመጣው የካርቦን ልቀት የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ኢትዮጵያ የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ልማት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ቢተው ሽባባውም ለችግኝ ተከላ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ ለእንክብካቤም ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።

ከግለሰብ ጀምሮ ሁሉም ተቋማት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች እንደ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ "ተክሎ  ማጽደቅን" ዓላማው አድርጎ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው ዓመት ከተተከሉት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች 79 በመቶው መጽደቁን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም