ለህዳሴው ግድብ ቀሪ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የድሬዳዋ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴው ግድብ ቀሪ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የድሬዳዋ ወጣቶች ገለጹ
ድሬዳዋ ፣ ነሐሴ 13 /2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀሪ ግንባታ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ገለጹ።
አስተዳደሩ ባዘጋጀው የስብዕና ግንባታ ስልጠና እየተሳተፉ የሚገኙት ወጣቶቹ እንዳሉት ለሀገር ሰላምና ልማት መረጋገጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።
ከመካከላቸውም የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት ነስረዲን ሸሪፍ በሰጠው አስተያየት "የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የህልውናችን መሰረት ነው" ብሏል።
መንግስት የተፈጠረበትን ጫና ተቋቁሞ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ማጠናቀቁ በሱም ሆነ በሌሎች ወጣት ዘንድ ደስታ መፍጠሩን ገልጿል ።
"ከቤተሰቤ ባገኘሁት ገንዘብ ለሶስት ጊዜ ቦንድ ገዝቻለሁ፤ ግድቡ የነገ ተስፋየን ዕውን የሚያደርግልኝ በመሆኑ በቀጣይም ቀሪውን የግንባታ ስራ ለማጠናቀቅ የሚጠበቅብኝን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ብሏል ።
የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን ኩራትና ህልውና መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ሰለሞን ኃይሉ ነው።
ወጣቱ ዕውቀትና ጉልበቱን በመጠቀም ራሱንና ሀገሩን ለመለወጥ ግድቡ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመላክቷል ።
የግደቡ ግንባታን ቀሪ ስራ ለመጨረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።
"የገጠር ልጅ ነኝ፣ ቤተሰቦቼ ለግድቡ ቦንድ የሚገዙት ነገ ከጭለማ ወደ ብርሃን እንደሚያሻግራቸው ስለሚያውቁ ነው " ያለችው ደግሞ ወጣት ሳሊያ አህመድ ናት፡፡
ለግደቡ ግንባታ የሚጠበቅባትን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግራለች።
ግድቡ የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በመለወጥ ለዜጎቿ ኩራትና ክብር የሚያጎናጽፋ በመሆኑ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወጣቶቹ አስታውቀዋል።
የአካባቢያቸውን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረጉ ጥረቶችን በመከላከልና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ጨምረው ገልጸዋል።
ዜጎችን እርስ በርስ ለማጋጨትና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረትን እንደሚያወግዙም አመልክተዋል።
በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ለ12 ቀናት በተዘጋጀው የስብዕና ግንባታ ስልጠና 3ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።