የሰላም ሚኒስቴር እና እርቀ ሰላም ኮሚሽን በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ሚኒስቴር እና እርቀ ሰላም ኮሚሽን በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) የሰላም ሚኒስቴር እና እርቀ ሰላም ኮሚሽን በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ሰነዱን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን እና የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ፈርመዋል።
ስምምነቱ በአቅም ግንባታ፣ በሃብት፣ በመረጃ ልውውጥ፣ በተሞክሮ ማካፈል እንዲሁም የግጭት መንስኤዎችን ማጥናት እና የሚፈቱበትን ሀሳብ ማቅረብ የሚያስችል ነው።
ብሄራዊ መግባባት እና የመሳሰሉት ሀላፊነቶች ሁለቱ ተቋማት የሚያገናኟቸው እና የሚያስተባብሯቸው በመሆኑ ይህንኑ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት መሆኑም ተነግሯል።
ሁለቱ ወገኖች በሚጋሯቸው ራዕዮችና ግቦች ዙሪያ በታቀደና በተቀናጀ ሁኔታ በመተባበር ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበትን በቆጠበ መልኩ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንዲችሉ ዓላማ ያደረገ ስምምነት መሆኑን ተገልጿል።
ከስምምነቱ በኋላ የሁለቱ ተቋማት ሃላፊዎች በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሁለቱ ተቋማት ተቀራርቦ መስራት ውጤት እንደሚያመጣ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ተቋሙ በሰላም እና እርቅ ዙሪያ ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ከሰላም ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነትም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ህብረት እና አንድነት እየተጠናከረ እንዲመጣ ለሚከናወኑ ተግባራት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን የሰላም አጀንዳ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
ከግጭትና ጥላቻ ይልቅ በይቅርታ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሁለቱ ተቋማት በጋራ መስራት ውጤት እንደሚያመጣም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።