የእንጦጦና የሸገር ፓርኮች ኢትዮጵያ ያልተነካ የቱሪዝም ሐብት እንዳላት ያሳያሉ - የውጭ አገር ዜጎች - ኢዜአ አማርኛ
የእንጦጦና የሸገር ፓርኮች ኢትዮጵያ ያልተነካ የቱሪዝም ሐብት እንዳላት ያሳያሉ - የውጭ አገር ዜጎች
አዲስ አበባ፣ ነሓሴ 13/2012(ኢዜአ) የሸገርና የእንጦጦ ፓርኮች የኢትዮጵያን ያልተነካ የቱሪዝም ሐብት እንደሚያሳዩ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎች አገራት ምሣሌ የሚሆን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሸገርና የእንጦጦ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን ይህም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይፋ ሆኗል።
በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት ቻይናዊያኑ ሚስተር ቻንግ እና ሚስተር ላምቦር ቼን ፓርኮቹን በአካልና በቴሌቪዥን የመመልከት ዕድል እንደገጠማቸው ይገልጻሉ።
የእንጦጦን ፓርክ በአካል ተገኝቼ መመልከት ችያለሁ ያሉት ሚስተር ላምቦር ቼን ፓርኩ የአገሬውንም ሆነ የትኛውንም የውጭ አገር ዜጋን ዓይን የሚስብ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያዊያንን ባሕል ሳይለቁ ግን ደግሞ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውም የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያዊያንን አኗኗር፣ ባህልና ትውፊት በቀላሉ እንዲረዱም ያደርጋሉ ብለዋል።
እነዚህ ፓርኮች ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን የሚያዝናኑባቸው፣ አንዱ ስለሌላው የሚማሩባቸውም ናቸው ያሉት ደግሞ ሚስተር ቻንግ ናቸው።
ፓርኮቹ የውጭና የውስጥ ቱሪዝምን በማሳደግ ለአገሪቷ ጠቃሚ የገቢ ምንጭ እንደሚሆኑ በመጠቆም ለቱሪዝሙ እድገት መሰል ፓርኮች ቢስፋፉ መልካም ነው ብለዋል።
ቻይናዊያኑ አዲስ አበባን ከማስዋቀብ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተይዞ እየተሰራበት ያለውን የካርቦን ልቀት የመቀነስና ችግኝ የመትከል ስራ በቁርጠኝነት እየሰራች ስለ መሆኗም መስክረዋል።
በየዓመቱ በክረምት ወራት የሚተከሉ ችግኞች ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ፕሮግራም ከመተግበር አኳያ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳዩም ጠቅሰዋል።
ይህ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆኑንና ሁሉም አገር ሊተገብረው እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።