ቀጥታ፡

የደብረታቦር በዓልን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) የደብረታቦር (ቡሔ) በዓልን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። በዓሉ "ደብረታቦርን በደብረታቦር" በሚል ለሶስተኛ ጊዜ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተከብሯል።

በዓሉ የሚከበረው ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ለደቀመዛሙርቱ ብርሀነ መለኮቱን መግለጹን መነሻ በማድረግ ቢሆንም በዓሉ በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊም ጭምር ነው።

በበዓሉ የፌዴራል፣ የአማራ ክልል፣ የደቡብ ጎንደር ዞን እና የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ምዕመናን ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው እንዳሉት ዘንድሮ በኮኖና ምክንያት ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም በዓሉ በመላው አገሪቱ በድምቀት እንዲከበርና አከባበሩን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ ነው።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምኅረቴ የደብረታቦር ወይም የቡሄ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ሲሆን ከሀይማኖታዊ ዳራው ባሻገር ባህላዊ ይዘት አለው ብለዋል።

የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው በዓሉን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀው ሕዝባዊ በዓል እንደመሆኑ ሕዝቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ እንዲያከብር አሳስበዋል።

የቡሄ በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 የሚከበር ሲሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሕፃናት በጭፈራ፣ እናቶች ዳቦ (ሙልሙል) በመጋገርና ሕዝቡም ችቦ በማብራት የሚያከብሩት በዓል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም