ቀጥታ፡

ኢትፍሩት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበልን ነው - ሸማቾች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) በኢትፍሩት ማዕከላት ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በጥራት እየቀረቡላቸው መሆኑን በማዕከላቱ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ሸማቾች ገለጹ።

ሸማቾቹ ማዕከላቱ በተለይ የፍራፍሬ ምርቶች ከገበያው ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያህል የዋጋ ቅናሽ እያቀረቡ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ቅኝት ባደረገባቸው የኢትፍሩት ማዕከላት ያነጋገራቸው ሸማቾች እንደሚሉት፤ በማዕከላቱ የሚያገኟቸው ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁና በትክክል የሚመዘኑ ናቸው።

አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይ የፍራፍሬ ምርቶች ከገበያው አንጻር በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

መላኩ ሊበን የተባለው አስተያየት ሰጪ "በጣም የኪሎ ልዩነት አለው፣ ዕቃዎቹም ጥራት አላቸው፣ በእጅ አይነካኩም። በዋጋም ጥሩ ናቸው ይበል የሚያሰኝ ነው።" ብሏል።

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በእህልና ቡና ግብይት ጣቢያዎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ማደራጃ ማከፋፈያ መጋዘኖችና በየፍጆታ ዕቃዎች መሸጫ ማደራጃ መደብሮች ውስጥም ምርቶችን እያቀረበ ይገኛል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እንዳሉት፤ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የማኅበረሰብ ክፍል አርሶአደሩ የሚያመርተውን እንዲሁም ከውጭ የሚያስገባቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ገበያን ለማረጋጋት ይሰራል።

ያነጋገርናቸው ሸማቾች በበኩላቸው ኢትፍሩት ምርቶችን በተለይ ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማቅረብ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበትና ከተደራሽነት አንጻርም ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኤደን ደበላ የተባለችው አስተያየት ሰጪ በበኩሏ "ለማኅበረሰቡ ኑሮ በጣም ተወዷል። በጣም ከብዶናል፤ በፖለቲካውም፣ በበሽታውም በጣም ከባድ ላይ ነው ያለነው። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ነገር በየአቅራቢው ቢኖር የተሻለ ነው። እና በጣም ለውጥ አለው። እንዲህ ዓይነት አማራጭ በብዛት ቢኖር ለኑሮ ማረጋጋቱ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ" ብላለች። 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በግብርናና በኢንዱስትሪ ምርቶች፣ መሠረታዊ ሸቀጦች ግብይት ለሸማቹ፣ አርሶ አደሩና አምራቹ የገበያ ዕድል በመፍጠር፤ ከሸማቹ ኅብረተሰብ ጋር በማስተሳሰር የአገር ውስጥ ገበያ ማረጋጋት ከተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማዎች ውስጥ ነው።

ኮርፖሬሽኑ 64 የእህልና ቡና ግብይት ጣቢያዎች፣ 105 አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ማደራጃ ማከፋፈያ መጋዘኖችና በሰባት የፍጆታ ዕቃዎች መሸጫ ማደራጃ መደብሮች ውስጥም ምርቶችን እያቀረበ ይገኛል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ግብይት ማዕከላቱም አትክልትና ፍራፍሬ፣ በፋብሪካ ደረጃ የተቀነባብሩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም የአትክልት ዘሮች ለሽያጭ ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም