ኢየሩሳሌም ህጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ለችግረኞች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢየሩሳሌም ህጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ለችግረኞች ድጋፍ አደረገ
ባህርዳር፣ ነሐሴ 12/2012(ኢዜአ)ኢየሩሳሌም ህጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በባህር ዳር ከተማ በኮሮና ቫይረስ ክስተት ተጽዕኖ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምግብና ሳቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች ኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ጠንካራ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በድርጅቱ የባህርዳርና አካባቢዋ ኃላፊ አቶ እደግልኝ ፈንታ ትናንት ድጋፉ በተበረከተበት ወቅት እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ክስተት አነስተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ድጋፍ እየተደረገ ነው።
በባህርዳር ከተማ ለ700 አካል ጉዳተኞች፣ ሴተኛ አዳሪዎችና ሌሎች ደጋፊ ለሌላቸው የችግሩ ተጋላጮች ድጋፉ መደረጉን ተናግረዋል።
ከተደረገው ድጋፍ መካከል ሳኒታይዘርና ሳሙና እንዲሁም የምግብ ዱቄት ፣ ማካሮኒና ዘይት፣ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በዘጌና አካባቢው ለሚኖሩ 400 ሰዎች ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
የድርጅቱ ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በበኩላቸው ድርጅቱ ባለፉት 35 ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህብረተሰቡን ችግር የመፍታት ስራ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ 35 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የወቅቱ ክስተት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ መካከልና ተጓዳኝ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የቫይረሱን ክስተት ተከትሎ ለችግር የተጋለጡ 650 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት እለታዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
"መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች ለተቸገረ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደርሱበት ወቅት አሁን ነው" ያሉት ደግሞ በክልሉ የኮሮና ሀብት ማሰባሰብ ግብረ ኃይል ተወካይ ዶክተር ፀጋ ጥበቡ ናቸው።
ክልሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ባለሃብቱንና ማህበረሰቡን በማስተባበር የቫይረሱን ክስተት ተከትሎ የተቸገሩ ሰዎች ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ እተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የእለት ምግብ አቅርቦት እጥረት እንዲከሰት ጥረት ማድረጉን ጠቁመው ችግሩን ለመሻገር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አጋርነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስዋል።
የኮሮና መከሰት ኑሮውን አስቸጋሪ እንዳደረገው የገለፀው ደግሞ የ11ኛ ክፍል ተማሪና አካል ጉዳተኛ ወጣት ፈንታሁን ገነት ነው።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሰውን ክብደት በሚዛን የመላክት አገልግሎት በመስጠት ህይወቱን ይመራ እንደነበር ጠቅሶ አሁን ላይ ስራ በማቆሙ ለችግር መጋለጡን ተናግሯል።
በወሳኝ ወቅት የተደረገለት ድጋፍ ችግሩን ለመቋቋም እንደሚያግዘው ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሰፊነሽ አለሜ በበኩላቸው የኮሮና ክስተት ተከትሎ ይተዳደሩበት የነበረው የቡናና ሻይ ንግድ በመቀዛቀዙ መቸገራቸውን አስረድተዋል።
"ድጋፉ የእለት ጉርሴን በመቻል አስቸጋሪውን ቀን እንድወጣ ያግዘኛል" ብለዋል።
በድጋፍ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት አመራሮችና ድጋፍ የተሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።