ቀጥታ፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው በጀት ዓመት ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው በጀት ዓመት 233 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው የተቋሙን ያለፈው በጀት አፈጻጸም እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስቴሩ ባለፈው በጀት ዓመት 270 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም  233 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 86 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካቱን ገልጸዋል።

ገቢው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ብልጫ አለው።

ከአገር ውስጥ ገቢ 128 ቢሊዮን ወይም 84 በመቶ፣ ከውጭ ንግድ ጉምሩክ 104 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ ከሎተሪ 152 ሚሊየን ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።

አመራሩና ሠራተኛው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ተግባብቶ በመሥራት፣ የቴክኖሎጂ (e-tax, አጠቃቀም፣ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻል፣ የታሪፍ ማሻሻያ፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር፣ ለግብር ከፋዮች ዕውቅና መስጠት፣ የዋጋ ትመና አሰራር ማሻሻያ የማድረግ ሥራ መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል። 


ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው አንጻር አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ሚኒስተሩ አብራርተዋል።

ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ የታክስ ጥመርታ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

በ2013 በጀት ዓመት 290 ቢሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ባለፈው አንድ ወር 21 ነጥብ 6 ቢሊዮን በመሰብሰብ የዕቅዱን 110 በመቶ መሳካት ተችሏል ብለዋል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም