የፀጥታ ኃይሉ የህዝብ ሰላምና ደህነነትን ከመጠበቁ በተጓዳኝ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ ኃይሉ የህዝብ ሰላምና ደህነነትን ከመጠበቁ በተጓዳኝ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ ነው
መተማ፣ ኢዜአ 13/12 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የህዝብ ሰላምና ደህንነትን ከመጠበቅ ጎን ለጎን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ህዝባዊ ወገንተኛነታቸውን እየተወጡ መሆኑን የፀጥታ ኃይል አባላት ተናገሩ፡፡
የፀጥታ አካላት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ ለወጣቶች ተጨማሪ አቅምና ወኔ እንደፈጠረላቸውም ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል ምክትል ሳጅን ገብሬ ባየ እንዳሉት የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ህብረተሰቡ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እየሰሩ ይገኛሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ በጉልበትና ገንዘባቸው አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በበጎ ፈቃድ ስራውም የአቅመ ደካሞችን የተጎዳ መኖሪያ ቤታቸውን በመጠገን እንዲሁም በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወጎኖችን የምግብ እህል እያገዙ በማደል ድርሻቸው እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እስካሁንም ከወር ደመወዛቸው በመቀነስ 200 ብር በማዋጣት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማዋላቸውን ጠቅሰው፤ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉበትም አመልክተዋል።
"በመንግስት ከተሰጠኝ ኃላፊነት በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ ህዝቤን ማገልገል መቻሌ ድርብ ኩራት እንዲሰማኝ አድርጎኛል" ያሉት ደግሞ በምድረ ገነት ከተማ የሚገኙት ሌላው የክልሉ ልዩ ኃይል ባልደረባ ዋና ሳጅን ጋሻው ደርብ ናቸው፡፡
ለችግር የተገላጡ ወገኖችን ገንዘባቸውን በማዋጣት የምግብ እህል እርዳታ እንዲያገኙ፣ የአቅሞችን ቤት እንዲጠገንና ማሳቸውን የማረም ስራ እንዳከናወኑ ተናግረዋል።
በገንዳ ውሃ ከተማ የልዩ ኃይሉ የሎጅስቲክ ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ዘመዴ ግርማ በበኩላቸው ከፀጥታ ስራቸው በተጓዳኝ ልዩ ኃይሉ በልማት ስራዎች በመሰማራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ህዝባዊ ወገንተኛነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮሮና ሳቢያ የተቸገሩ ሰዎች በገንዘብ በመደገፍ፣ አቅመ ደካማ ለሆኑት ደግሞ በጉልበት በማገዝ እየደረገፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከህብረተሰቡ ጋር የሚኖራቸውን መልካም ግንኙነት ከማሳደጉም በላይ ወንጀልን ለመከላከል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የፀጥታ አካላት በቀጥታ ገንዘብ መዋጮ ከ60 ሺህ ብር በላይና በጉልበት ተሳትፎ ደግሞ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ የማህበራዊ ልማት መምሪያ የወጣቶች ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ተገኘ ጌታቸው ናቸው፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የፀጥታ አካሉ ተሳትፎ ማድረግ ለወጣቶች ተጨማሪ አቅምና ወኔ እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
"ችግኞችን መትከል፣ የድሃ ድሃ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ቤት መጠገንና የተዘራላቸውን ሰብል ማረም በዋናነት በፀጥታ አካሉ የተሰሩ ስራዎች ናቸው" ብለዋል፡፡
በዞኑ ከ340 ሄክታር መሬት በላይ በሰብል የተሸፈነ ማሳ የአረም ማረም ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 40 ሄክታር የሚሆነው በፀጥታ አካሉ የተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም በዞኑ 40 ቤቶች የመጠገንና ሌሎች 10 ቤቶችን ደግሞ እንደ አዲስ የመገንባት ስራ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሰራቱን ገልፀው በሁሉም የፀጥታ አካሉ ተሳትፎ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በተያዘው የክረምት ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስራ መከናወኑን አስተባባሪው አስታውቀዋል።