የኢትዮጵያን አቪየሽን ለማዘመን የግል አየር መንገዶችን ማበረታታት እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን አቪየሽን ለማዘመን የግል አየር መንገዶችን ማበረታታት እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 12/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግና የአቪየሽን ዘርፉን ለማዘመን የግል አየር መንገዶችን የሚደግፍና የሚያበረታታ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን የትራንስፖርት ካውንስል አስታወቀ።
በከተማ ባቡር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየታዩ ያሉ ክፍተቶች እንዲታረሙም ተጠይቋል።
የትራንስፖርት ካውንስል የ2012 በጀት የክትትልና ድጋፍ አፈጻጸም ሪፖርቱን በዛሬው እለት ለባለድርሻ አካላት አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ካውንስሉ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በጥር 2012 ዓ.ም 9 አባላት ያሉት የዘርፉ ተዋንያንን በአባልነት ይዞ መቋቋሙ ይታወሳል።
ካውንስሉ ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎም በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ካሉ 10 ተጠሪ ተቋማት መካከል አራቱ ላይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ያከናወናቸውን ተግባራት አቅርቧል።
የካውንስሉ ጸሃፊ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ፋንታሁን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶችን የሚደግፍና የሚያበረታታ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአቪየሽን ዘርፉ ማነቆ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረትና ለግል አውሮፕላኖች የጥገና ማእከል አለመኖሩ መሆኑም ተነስቷል።
ካውንስሉ በመንጃ ፍቃድና በሰሌዳ አሰጣጥ፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ የፋይናንስ አማራጮችን ከመፈለግ አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቅሷል።
በተለይ በከተማ ባቡር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየታዩ ያሉ ክፍተቶች በአፋጣኝ ሊታረሙ እንደሚገባ ነው በሪፖርቱ ያመለከተው።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ካውንስሉ ከተቋቋመ ጀምሮ በተለይ በትራንስፖርት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና ዘርፉን ለማገዝ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል።
ካውንስሉ በዘርፉ ተዋንያን መዋቀሩም የክትትልና የድጋፍ ስራውን ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የግሉ ዘርፉ እንዲሰማራ ለማድረግ መታሰቡንም አንስተዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በሚተገብራቸው ፕሮጀክቶችና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የግሉን ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ ይፈልጋል።