ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የምርመራ መዝገብ ግልባጭ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ብይን ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የምርመራ መዝገብ ግልባጭ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ብይን ሰጠ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 12/2012 (ኢዜአ) በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ጉዳይ በተጠረጠሩት እነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የምርመራ መዝገብ ግልባጭ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ብይን ሰጠ።
በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ቁጥር 215730 የቀረቡት አቶ እክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ወይዘሮ ቀለብ ስዩም ላይ ቀሪ ሁለት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሰምተዋል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ዐቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩለት ያቀረባቸው 1ኛ እና 2ኛ ምስክሮች ቀርበው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ምስክርነት የመስማት ሂደቱ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎች የቀረበባቸው ማስረጃ የዋስ መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሆነው ጉዳዩን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ እንዳለው በመግለጽ፤ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የማያሰጥ በመሆኑ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ክስ እስኪመሰርት ድረስ ተጠርጣሪዎች በማረፊያ ቤት ቆይተው እንዲጠባበቁ ጠይቋል።
የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ያሰማው ማስረጃ ይጠፋብኛል ብሎ ባሰባቸው ምስክሮች ላይ ብቻ እንደሆነም አመልክቷል።
ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ የተሰሙት የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ቃል ከመቅረጸ ድምጽ ወደ ኮምፒውተር ተገልብጦ ከመዝገብ ጋር እንዲያያዝ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የተጠረጠሩበት ወንጀል የሰው ህይወት የጠፋበትና ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ ክስ እስኪመሰረት ድረስ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ አዟል።
ዐቃቤ ህግ የምርመራ መዝገብ ግልባጭ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርትም ፍርድ ቤቱ በይኗል።