ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለጤና ተቋማት የ9 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች

ነሐሴ 12 / 2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን  ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ   ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ እና አልባሳት  ድጋፍ አደረገች

ድጋፉም 200ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ  ጭምብሎች፣200ሺህ  የእጅ ጓንቶች፣18ሺህ ህክምና አልባሳት ያካተተ ነው 

ቤተክርስቲያኗ ድጋፉን ያደረገችው   በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ፣በትግራይ ክልሎችና አዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ  90 የጤና ተቋማትና 18 የአረጋውያን ማቆያዎች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀጳጳስ  ድጋፉ ዜጎችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ቅድሚያ ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑት ለጤና ባለሙያዎች  መደረጉን ገልጸው ምዕመናን በቤታቸው ሆነው በመፀለይ ወረርሽኙን እንዲያሳልፉ  መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ (ዶክተር)ቤተክርስቲያኗ ድጋፉን ያደረገችው የ23 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት በመቅረጽ ካገኘችው ድጋፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

እስከ ጥቅምት ድረስ የሚቆየው ፕሮጀክት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ  ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው የክልል ተወካዮች ባደረጉት ንግግርም ቤተ ክርስቲያኗ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ድጋፉ ወረርሽኙን ከመከላከል አኳያ የነበረባቸውን እጥረት እንደሚያቃልላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን  ከዚህ በፊት  ከ1500 በላይ  የእጅ ንፅህን መጠበቂያዎች፣ 16ሺህ 500 ሊትር አልኮል፣ 3ሺህ500 ሳኒታይዘር ፣200 ሊትር ፈሳሸ ሳሙና ለጤና ተቋማት ማሰራጨቷን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን 148 የጤና ባለሙያዎችን   አሰልጥና ወደስራ ማስገባቷና ለምዕመናን በሬዲዮና በአካል የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠቷ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም