ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በጎርፍ ውሃ የተከበቡ ወገኖችን በሄሊኮፕተር የማውጣቱ ስራ በስኬት ተጠናቀቀ

ሰመራ፣ ነሐሴ 12/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል በጎርፍ ተከበው የነበሩ ወገኖችን በሄሊኮፕተር ታግዞ የማውጣቱ ስራ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢፌዴሪ መከላከያ እና አየር ኃይል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የመከላከያ እና አየር ኃይል አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት እንዳላቸውም ተመልክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን እንደገለጹት፤ በክልሉ ዘንድሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በአዋሽ ዳር የሚገኙትን ጨምሮ በ11 ወረዳዎች ከ67ሺ ሰዎች በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ክእነዚህ ውስጥ ከ40 ሺ 700 በላይ ሰዎች በጎርፉ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

ብዛት ያላቸው ሰዎችም በጎርፍ ውሃ ተከበው ለአደጋ ተጋልጠው እንደነበር አውስተዋል።

ክልሉ ከኢፌዲሪ መከላከያ እና አየር ኃይል ጋር በመተባበር ላለፉት አስር ቀናት በሄሊኮፕተሮች በመታገዝ በውሃ ተከበው የነበሩ ሰዎችን የማውጣትና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የማድረሱ ስራ በትጋት ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም በአሳኢታ፣ አፋምቦ እና ገረኒ ወረዳዎች በውሃ ተከበው የነበሩ 4 ሺ 915 ሰዎችን በሁለት ሄሊኮፕተሮች በመታገዝ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲወጡ በማድረግ ትናንት በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን አቶ መሐመድ አስታውቀዋል።

3 ሺህ 640 ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ በደራሽ ጎርፍ ተከበው የነበሩባቸው አካባቢዎች መከላከያ እና አየር ኃይል አስቸኳይ ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ ተከስቶ በነበረው የጎርፍ ውሃ ምክንያት አንድም የሰው ህይወት እንዳይጠፋ በተለይ የምስራቅ ዕዝ አየር ኃይል አባላት የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል።

የሰራዊቱ አባላት እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ወገናቸውን ለመታደግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት ያላቸው መሆኑን አቶ መሐመድ አስታውቀዋል።

የተለያዩ ክልሎችም በጎርፉ ለተጎዱ ወገኖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም