ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰች ነው --ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 12/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿን ለማስፋት እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን አስታወቀ።

አገሪቱ የጅቡቲን ወደብ በዋነኝነት እየተጠቀመች መሆኗ ይታወቃል።

አገሪቱ  እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ንግዷን የምታከናወነው በዚሁ ወደብ ነው።

በዚህም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ባማከለ መልክ ተጨማሪ ወደቦችን ማልማትና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ባለስልጣኑ ይገልጻል።

ኢትዮጵያ አማራጭ ወደብ ስለሌላት በኮንቴይነር ከውጭ ለማስገባት ከ700 እስከ 800 ዶላር ትከፍላለች።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አገሪቱ የምትጠቀማቸው ወደቦች ውስን በመሆናቸው ተጨማሪ ወደቦችን ለመጠቀም ጥረት እያደረገች ነው።

በዚህም በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የሚገኙ አካባቢዎች ለየትኛው የባህር ወደብ ይቀርባሉ የሚለውን ቅድሚያ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። 

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ወደብ ብቻ መጠቀም በውድድር የሚገኙ ጥቅሞችን ከማጣት ጀምሮ የመደራደር አቅምን እስከማዳከም ድረስ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል። 

በመሆኑም የእያንዳንዱ ዕቃ መነሻና መድረሻ ቦታ ከወደብ ያለውን ርቀት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ተመራጭ እንደሆነ አስረድተዋል።

አገሪቱ እስካሁን ድረስ በተለይ የበርበራና የፖርት ሱዳንን ወደቦችን ለመጠቀም የተደረሰው ስምምነት ውጤታማ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በሚቀጥሉት ጊዜያት የወደቦቹን አጠቃቀም በማሻሻል እንደሚሰራ አቶ መኮንን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ልትጠቀምባቸው የምትችልባቸውን ወደቦች ኤርትራና ኬንያ ውስጥ እያፈላለገች መሆኗን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በጅቡቲ የሚገኘውን ታጁራ ወደብን ለመጠቀም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ሰባት ወደቦችንና 12 ኮሪደሮችን በመጠቀም የወደብ አማራጮችን ለማስፋት ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም