ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ሙላቱ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኦስትሪያ አምባሳደር አሰናበቱ

አዲስ አበባ  አምሌ 5/2010 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር አንድሪያስ ሜላንን አሰናበቱ። ፕሬዝዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። ሁለቱ አገራት ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ እስካሁን ድረስ የዘለቀ ወዳጅነት ቢኖራቸውም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያህል በንግድና ኢንቨስትመንት ይህ ነው የሚባል ትስስር እንዳልነበራቸው ተገልጿል። ፕሬዝዳንት ሙላቱ ቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የኦስትሪያ አምባሳደር ሁለቱ አገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት መግለፃቸውን የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል። ኦስትሪያዊያን በትምህርትና በቴክኖሎጂ ምርቶች ያላቸውን ልምድና አቅም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት መልካም ተጽዕኖ ማሳረፍ እንደሚኖርባቸው ነው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ለተሰናባቹ አምባሳደር ጥሪ ያስተላለፉት። አምባሳደር አንድሪስ ሜላን በበኩላቸው በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያና የኦስትሪያን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል። ኦስትሪያ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩትን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ጠቁመው የተጀመረው ሰላም በአገራቱ መካከል የዜጎች የጋራ ህልም የሆነው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ትስስር ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥም ዋስትና ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት የቆዩት አምባሳደር አንድሪስ ሜላን በቆይታቸው ድጋፍ ላደረጉላቸው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም