ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ ውጭ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች ማስቀመጥ ተከለከለ - ኢዜአ አማርኛ
ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ ውጭ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች ማስቀመጥ ተከለከለ
አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በግለሰቦች ወይንም በኩባንያዎች ከባንክ ውጭ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ማስቀመጥ መከልከሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ ግለሰቦች ወይንም ኩባንያዎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ ውጭ ማስቀመጥ መከልከሉን ይፋ አድርገዋል።
የመንግስትም ሆኑ የግል ባንኮች ከውጭ አበዳሪ ተቋማት በዶላር መበደር ይችላሉም ተብሏል።
ይህ አሰራር ደግሞ በአገሪቱ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል ይረዳል ብለዋል።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም ወደ ባንክነት ማደግ የሚችሉበት መመሪያ መውጣቱን ዶክተር ይናገር ይፋ አድርገዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርአትን ለማሳለጥ ሲባል ከባንኮች በተጨማሪ ሌሎች ፋይናንሻል ያልሆኑ ተቋማትም በክፍያ ስርአት ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ በመግለጫው ተመልክቷል።
ተቋማቱ ከብሄራዊ ባንክ ፈቃድ ወስደው በኤቲኤም፣ በፖስ ማሽን እንዲሁም ሌሎች አማራጮች የክፍያ ስርአት ላይ መሳተፍ ይችላሉም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የብር ኖቶች ላይ መፃፍም ሆነ ስእል መሳል የተከለከለ ስለመሆኑም ዶክተር ይናገር ገልጸዋል።