ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ ቁጥር ጨመረ

ነሀሴ 11/2012 (ኢዜአ) በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹ በሚሰጠው ሳምንታዊ መደበኛ የበረራ አገልግሎት ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

ማሻሻያውም እያደገ የመጣውን የደንበኞች የጉዞ ፍላጎት ለማሟላት ያለመ ነው።

አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው፣ እያደገ ለመጣው የደንበኞቻችን የጉዞ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አሁን በምንበርባቸው የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቻችን የነበረውን መደበኛ ሳምንታዊ የበረራ አገልግሎት ቁጥር ጨምሯል።

የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የተደረገውን የአገልግሎት መሻሻል አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ "የበረራውን ቁጥር በመጨመራችን ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል" ብለዋል።

አክለውም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የመከላከያ እርምጃዎችን በጥብቅ ዲሲፕሊን በአየር ማረፊያም ሆነ በበረራ ወቅት ተግባር ላይ ማዋሉን ተናግረዋል።

በዚህም የቫይረሱን ስርጭት እየተከላከልን የደንበኞቻችንን እና የሰራተኞቻችንን ደህንነት በመጠበቅ አገልግሎታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል አየር መንገዱ በመግለጫው።

አየር መንገዱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን በመከላከል የመንገደኞቹንና የሰራተኞቹን ጤንነት ለመጠበቅ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች ደንበኞች ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል።

በመሆኑም መንገደኞች በአየር መንገዱ ይፋዊ ድረ ገጽ፣ ቻት ቦት፣ ኢሜይል፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ እንዲሁም በአየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የጥሪ ማእከልና የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አማካኝነት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብሏል።

በእነዚህ የዲጂታል አማራጮች የሚቀርቡ አገልግሎቶች ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አብረው የሚሄዱ ከመሆናቸው ባሻገር፣ የደንበኞችን ፍላጎት ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸውም ብሏል።

ደንበኞች በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ የበረራ ትኬታቸውን ተመዝግበው ሲገዙ የ10 በመቶ የትኬት ቅናሽ እንደሚያገኙ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም