ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ በዓለም አቀፍ ስምምነትና በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ ድጋፎችን እያስገኘ ነው--ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ነሓሴ 11/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በዓለም አቀፍ ስምምነት፣ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና በቴክኖሎጂ ድጋፎችን እያስገኘ መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የአካባቢ ውሎችን ለመተግበር የሚያስፈልጉ ፖሊሲዎችን፣ ስልቶችን፣ ሕጎችንና መርሃግብሮችን ያዘጋጃል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በብዝሃ-ህይወት እንክብካቤ እና በርሃማነትን በመከላከል ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማለች።

ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የሚያጠናክሩና ግቡን እንዲመታ የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት ሁሉም ስምምነቶች አገራት ድንበር ተሻጋሪ ችግሮችን በአንድነት ለመፍታት የሚያስችሉ ሲሆን ለኢትዮጵያም በስምምነቶቹ ላይ የመደራደር እድል ይፈጥርላታል።

በዚህም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ለችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ድሃ አገራት የቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ በቀዳሚነት እየሰራች መሆኗን ፕሮፌሰር ፍቃዱ ጠቁመዋል።

 ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በዓለም መድረክ እያካሄደች ያለው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ለምትጫወተው ሚና በጎ ምላሽ እያስገኘ ነው።

ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን አርአያነት ለመከተል ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንም ነው ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጭ ተቋማት የድጋፍ ፕሮፖዛል አስገብታ በአሁኑ ወቅት አወንታዊ ምላሽ እያገኘች መሆኑንና ውጤቱ በቀጣይ ስድስት ወራት እንደሚታወቅ አመልክተዋል።

 የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል የሚሰራው ሥራ መጠናከር ሀብት እንዲንቀሳቀስ ከማገዙ ባለፈ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል ያግዛል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ሥራዋ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች ትገኛለች።

መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በማንቀሳቀስ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደተግባር መገባቱም የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም