የብልፅግናው ጉዞ እንዳይቀለበስ ወጣቱ በግንባር ቀደምትነት ሊታገል ይገባል - ሊጉ - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግናው ጉዞ እንዳይቀለበስ ወጣቱ በግንባር ቀደምትነት ሊታገል ይገባል - ሊጉ
ሀዋሳ፣ ነሐሴ 11/2012 (ኢዜአ) የለውጡና ብልፅግናው ጉዞ በየትኛውም የሁከት አጀንዳ እንዳይቀለበስ ወጣቱ በግንባር ቀደምትነት ሊታገል እንደሚገባ የፌዴራል ብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ አሳሰበ።
የሊጉ ፕሬዚዳንት ወጣት አስፋው ተክሌ ለኢዜአ እንደገለጸው ወጣቱ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ በነበረበት ሁኔታ ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስ አንዳንድ አካላት ባቀነባበሩት ሴራ ሃገሪቱን ለማበጣበጥ ሞክረዋል።
ሙከራው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች መስዋዕት የከፈሉለት የለውጥ ሂደት በየትኛውም የጥፋት እንቅስቃሴ ሊቀለበስ እንደማይቻል መንግሥት በወሰደው እርምጃ በተግባር ማሳየቱን ተናግሯል።
እኛ ወጣቶች የተሰራ ሃገር የምንረከብ ብቻ ሳንሆን በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሚናችንን የምንወጣ መሆናችንን በማሳየት ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገባል ብሏል።
የተገነቡ የልማት አውታሮች ከአጥፊዎች በመጠበቅ የህዝቦች አለኝታና መመኪያ መሆኑን በስራ ማሳየት ከሁሉም ወጣቶች እንደሚጠበቅ ወጣት አስፋው ገልጿል።
ከውጭና ውስጥ የተለያየ የጥፋት ተልዕኮ በማንገብ በሃገሪቱ ላይ እውን ለማድረግ በሚሸረበው ሴራ በዋናነት ተጎጂ የሚሆነው እራሱ ወጣቱ መሆኑን አውቆ በግንባር ቀደምትነት ሊታገል እንደሚገባም አሳስቧል።
ፅንፈኛው በተለያየ ጊዜ ወጣቱን ተጠቅመው ውድመት ለማድረስ እንደሚሞክሩ ያመለከተው የሊጉ ፕሬዚደንት ይህን ለመቀልበስ ወጣቱ ነቅቶ በተደራጀ አግባብ ለሠላምና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ዘብ ሊቆም እንደሚገባም መልዕክቱን አስተላልፏል።
የፓርቲው የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ሁሳ በበኩላቸው በቅርቡ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጸመው ጥፋት መንስኤው ፀረ ሠላም ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆኖ ለአጥፊዎች ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩትን በመለየት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በቀጣይ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም ፓርቲው ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሀሰን "በየክልሉ እየተደረገ ባለው ኮንፍረንስም ችግሩ እየጠራ ነው "ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኘው መዋቅር የህግ የማስከበር ስራውን በማስቀጠል የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በማንም ኃይል ሊያቆመው እንደማይችል ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል።
በፓርቲው ጽህፈት ቤት ፣ በሴቶች ፣ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተገኘ አንድ ሚሊዮን 600ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ በቅርቡ በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማስረከባቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።