ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ለዓለም አቀፍ ተልዕኮ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች ሊያሰማራ ነው

 አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለዓለም አቀፍ ተልዕኮ ያሰለጠናቸውን ከ180 በላይ የፖሊስ መኮንኖችኝ በተለያዩ ተልዕኮዎች ሊያሰማራ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

በ1939 ዓ.ም 'አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ' በሚል ስያሜ የተመሰረተው የዛሬው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢትዮጵያ ብቸኛው የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው።

በዩኒቨርርሲቲ ኮሌጁ የሰላም ማስከበር ስልጠናና ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክተር ኢንስፔክቴር ጎሳዬ ታደሰ ኮሌጁ ከፌዴራልና ክልል ፖሊስ ሠራዊት አባላት በተጨማሪ በመንግስታቱ ድርጅት ስር በተለያዩ አገራት ልዩ ልዩ ተልዕኮዎች የሚሰማሩ የፖሊስ መኮንኖችንም እያሰለጠነ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ማሰልጠኛ ተቋሙ አንጋፋ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተሳትፎው ግን ዝቅተኛ እንደነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት የፖሊሲ የመመሪያ ማሻሻያዎችን በማድርግ ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተሳትፎውን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።


ማዕከሉ በዋናነት የሰላም ማስከበርና አጫጭር የውጭ አገር ስልጠናዎችን ይሰጣል።

በዚህም በቅድመ ስምሪት ስልጠና የወሰዱ በመንግስታቱ ድርጅት ተልዕኮ የሚሰማሩ 'ፎርምድ ፖሊስ ዩኒት' በመባል የሚታወቁ  የፖሊስ መኮንኖችን ያሰለጥናል።

'ፎርምድ ፖሊስ ዩኒት' በተናጠል የማይቻሉ የሰላም ማስከበር ተግባራትን ለአብነትም የህዝብ ስርዓት ስምሪት፣ በመንግስታቱ ድርጅት ሠራተኞችና ተቋማት ጥበቃ ስራዎችንን ያካተተ ነው።

በኢትዮጵያም በዚህ መስክ የሰለጠኑ 180 የፖሊስ ኦፊሰሮች ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለስምሪት መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ በቅርቡም እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሰልጣኝ ፖሊስ መኮንኖች የሚሰማሩት አብዬ ግዛትን ጨምሮ በመንግስታቱ ድርጅት ስር ባሉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቦታዎች ነው።

ተልዕኳቸውም በሕዝብ ስምሪትና በመንግስታቱ ድርጅት ስር ባሉ ቦታዎች እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ደረጃውን የጠበቀ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት የፖሊሲና የመመሪያ ሪፎርሞችን በማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂና በሥነምግባር የታነጹ የፖሊስ መኮንኖችን ለማፍራት እየሰራ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።

ለዚህም ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትብብር በማድርግ ስልጠናዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጠል የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ "ተቋሙን በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ከዚህ በፊት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማሩ መኮንኖች ከሌሎች አገራት የተሻለ ግዳጅ አፈጻጸም እንደነበራቸው አስታውሰው፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በኩል ያሉ ውስንነቶችን ለማሻሻልም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም