ለሀገር አቀፍና የክልል የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ግብረ ኃይል የኮሮናን ሥርጭት ለመግታት የሚያግዝ ሥልጠና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር አቀፍና የክልል የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ግብረ ኃይል የኮሮናን ሥርጭት ለመግታት የሚያግዝ ሥልጠና ተሰጠ
ነሐሴ 11/2012 (ኢዜአ) ለሀገር አቀፍና የክልል የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ግብረ ኃይል የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመግታት የተጀመረውን "ማህበረስብ አቀፍ ንቅናቄ እና የምርመራ ዘመቻ" ለማሳካት የሚያግዝ የሥልጠና መድረክ በአዳማ ተሰጠ።
የሥልጠና መድረኩ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች ለተወከሉ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የኮሮናን ቫይረስ ሥርጭት ለመግታት በአዲስ መልክ የተጀመረውን ዘመቻ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሥልጠናው ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሰክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትክክል በማስተግበሩ በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።
አቶ ንጉሡ አያይዘውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባደረገው ጥናትና የመስክ ምልከታ በኅብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋትና በአስፈጻሚው አካል ባለው ቸልተኝነት አዋጁ መጣሱን አረጋግጧል ብለዋል።
የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች በሚጥሱት አካላት ላይ ለሕዝብ ደህንነት ሲባል የእርምት እርምጃ በመውሰድ የባሕሪ መጓደል ሁኔታዎች ማስተካከል አለብን ብለዋል።
አሁን እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ኅብረተሰቡ አካባቢ የታየውን የአስተምሮ መጓደል ማረም እንደሚገባም አቶ ንጉሡ አመልክተዋል።
ስለ በሽታው በማወቅና በመገንዘብ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ጥሩ ቢሆንም በሽታውን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎች እየተተገበሩ እንዳልሆነ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል።
እስካሁን በሽታውን ለመከላከል የተከናወኑት ተግባራት የቫይረሱ ሥርጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መርዳቱን የተናገሩት አቶ ንጉሡ የነበረው የአስተምህሮ ሂደትን በመለወጥ በኅብረተሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ሥራ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ለኅብረተሰቡ ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ራሱን እንዲጠብቅ መገናኛ ብዙሀን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
ሥልጠናው አሁን የተጀመረውን የምርመራና ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻን ግቡን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት በሙያቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን ዶክተር ተገኔ አስረድተዋል።
ሥልጠናው ለቀጣይ የኮቪድ -19 ማስተማሪያ ዘይቤውን ለመፈተሽ፣ የጎደለውን ለመለየትና ችግሩን ለመፍታት እንዲሁም የተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ለማሳካት እንደሚያግዛቸው ሠልጣኞች መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ አመልክቷል።