ቀጥታ፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎታቸው ጨምሯል - አምባሳደር መሐመድ ሳሌም አልራሽዲ

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 11/2012 (ኢዜአ) የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር መሀመድ ሳሌም አልራሽዲ ገለጹ።

የጤናው ዘርፍ ወደፊት የሁለቱ አገራት ዋንኛ የትብብር መስኮች ውስጥ አንዱ ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር መሀመድ ሳሌም አልራሽዲ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋነኛ የኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛና በማደግ ላይ የሚገኝ የገበያ አቅም ያላት መሆኗንም ተናግረዋል።

ሰፊ ብዝሃ ሀብት እና በጤና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በቴሌኮምዩኒኬሽንና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ያለው እምቅ አቅም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚጋብዝ መሆኑንም ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

"የአገሪቷ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት እየተካሄዱ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና የግሉ ዘርፍ በተለያዩ መስኮች እንዲሳተፍ እየተከናወነ ያለው ሥራ ለፍላጎቱ መጨመር ምክንያት መሆኑንም አምባሳደር መሀመድ ገልጸዋል።

እየተደረጉ ያሉት ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የምትችል ተመራጭ መዳረሻ አገር እንዳደረጋትም አመልክተዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ በርካታ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል።

ለዚህም "ጁልፋር የመድኃኒት ፋብሪካ" ፣ "አል ጉራይር አልሙኒየም ግሩፕ" እና የ"ፋልኮን ኢንዱስትሪ"  ኩባንያዎችን አምባሳደር መሐመድ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪካዊና በመተማመን፣ በመከባበርና በጋ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሁለቱ አገራት ግንኙነት በአስገራሚ ሁኔታ አድጓል፤ ይህም ግንኙነቱ በፍጥነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ብለዋል አምባሳደር መሐመድ።

ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የደህንነት መስኮች ትብብር እንዳላቸውና የሚደረጉ የልማት ድጋፎችም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች "ፈንድ ፎር ኢንተርፕራይዝ ዴቨሎፕመንት" ተቋም ጋር ከ200 ሺህ በላይ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን የሚያግዝ የ100 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

"ብድሩ በረጅም ጊዜ የሚከፈል መሆኑንና የወጣቶችና ሴቶች ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ነው" ብለዋል አምባሳደሩ።

ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን በተለይም በማህበራዊ፣ ባህላዊና ቱሪዝም መስኮች ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አዳዲስ የትብብር መስኮችም በመመልከት የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማስተዋወቅ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

"የጤናው ዘርፍ ወደፊት የሁለቱ አገራት ዋንኛ የትብብር መስኮች ውስጥ አንዱ ይሆናል" ብለዋል።

ከዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ45 በላይ አገራት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ነው አምባሳደር መሐመድ ያስታወቁት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ የመጣ ሲሆን ለዚህም በሁለቱ አገራት መሪዎች የሚደረጉ የሥራ ጉብኝቶች ምክንያት እንደሆኑ ይገለጻል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ አገራቱ የ3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በኤክስፖርቱ ኢትዮጵያ ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቡና፣ አትክልቶች፣ የጥራጥሬ ምርቶች እንዲሁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋዕጽዎች ስትልክ ማሽነሪዎች፣ ማዳበሪያ፣ የፍጆታ እቃዎችና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን  ወደአገር ውስጥ ታስገባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም