ቀጥታ፡

በሊባኖስ የሚኖሩ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃድ አገኙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11/2012 (ኢዜአ) በሊባኖስ የሚኖሩ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃድ ማግኘታቸው ተገለጸ።

በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ቆንሉ ጀነራል ተመስገን ዑመር ጽሕፈት ቤቱ በሊባኖስ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች መረጃዎች ለአገሪቱ ኢምግሬሽን ጉዳዮች መሥሪያ ቤት አስገብቶ እንደነበር ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚሁ መሠረት የኢሚግሬሽን ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል።

ከተመላሾቹ ኢትዮጵያውያን በቤይሩት የወደብ ፍንዳታ ምክንያት በመጠለያ ውስጥ ያሉ እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።

ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎችን ዝርዘር በቀጣይ ቀናቶች ውስጥ እንደሚያሳውቅ ጠቁመው፤ የሚመለሱት ዜጎች የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው የሚሸፍኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

''በስምንተኛው ዙር የሥም ዝርዝራቸውና መረጃቸው ተልኮ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያውን አሉ'' ብለዋል አቶ ተመስገን።

በሊባኖስ ሕግ ወንጀል የሰሩ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ያለባቸው፣ ከአሰሪዎቻቸው ጋር ውል ያልጨረሱና በሌሎች ምክንያቶች ዜጎች የመመለሻ ፈቃድ እንደማያገኙ ገልጸዋል።

ይሁንና በሊባኖስ አሁን ካለው አሳሳቢ ሁኔታ አንጻር በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያውያኑ ፈቃድ አግኝተው እንዲመለሱ ለኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤቱ ጥያቄ እንደሚቀርብ አመልክተዋል።

ዜጎቹ ለመመለስ ፈቃድ ቢያገኙም የመውጫ ቪዛ ለማግኘት ከሁለት እስከ ሦስት ወር እንደሚፈጅ ተናግረው፤ በፍጥነት ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

ጉዳዩ ከቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ አቅም በላይ የሚሆን ከሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጥያቄ እንዲቀርብ ሊደረግ እንደሚችል ነው አቶ ተመስገን ያስረዱት።

ጽሕፈት ቤቱ በዘጠነኛው ዙር ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ ባቀረበው ጥሪ መሠረት 3 ሺህ 300 ዜጎች መመዝገባቸውንና መረጃቸውም ወደ ሊባኖስ ኢምግሬሽን ጉዳይ መሥሪያ ቤት መላኩን ጠቁመዋል።

በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በሊባኖስ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 2 ሺህ 300 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል።

በራሳቸው ወጪ ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ዜጎች ካሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደርግላቸው አብራርተዋል።

ከቤይሩት የወደብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 360 ከፍ ማለቱን ነው አቶ ተመስገን የገለጹት።

ቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ በቤይሩት ከሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገዳም ጋር በመነጋገር 36 ኢትዮጵያውያን በገዳሙ መጠለያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በሊባኖስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኞች በመጠለያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ አገልግሎት ለማግኘት መጥታ የነበረች ኢትዮጵያዊ ምርመራ ተደርጎላት የኮሮናቫይረስ በምርመራ እንደተገኘባት ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

በቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ሁሉም ሠራተኞች ላይ በተደረገ ምርምራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል። በጽሕፈት ቤቱም የኬሚካል ርጭት ተደርጓል ብለዋል።


ኢትዮያውያን ወደ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ሲመጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒተይዘር) በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።


በአጠቃላይ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያግዙ የጥንቃቄ መልዕክቶች ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ አቶ ተመስገን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም