በአፍሪካ የሕክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ሥርአት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የሕክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ሥርአት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል
ነሓሴ 11/2012(ኢዜአ) በአፍሪካ የሕክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ስርአት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል።
በዙም መተግበሪያ የሚካሄደው ስብሰባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ወጪና ገቢ ባንክ (አፍሪኤግዚም ባንክ)፣ የአፍሪካ የበሽታ መቆጠጣርና መከላከል ማዕከል፣ የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ስትራይቭ ማሲዪዋ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ጋር በመሆን ያዘጋጁት ነው።
የአፍሪካ የሕክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ስርአት የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በሆኑት ስሪል ራማፎሳ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።
ስርአቱ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጓቸውን የሕክምና ቁሶች በዲጂታል መንገድ መግዛት የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው።
የነገው ስብሰባ የግዢ ስርአቱ በሚያስገኘው ጠቃሜታና አጠቃላይ አደረጃጀቱ ላይ ያተኮረ እንደሆነ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በተለይም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገራት በቀጠናው የሚገኙ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችና ሌሎች ወደ ግዢ ስርአቱ በመግባት ጥቅም ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ገልጿል።
በስብስባው ላይ በአፍሪካ የህክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ስርአት ላይ ገለጻ ተደርጎ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በኢጋድ የተቀናጀ የመድኃኒቶች ቁጥጥር ኢንሺዬቲቭ እና የኢጋድ የሕክምና አቅርቦቶች የግዢ ስርአት ለማቋቋም እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግም ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።
በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብአቶችን በፍጥነትና ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ ለማግኘት የግዢ ስርአቱ ወሳኝ ሚና አለው ተብሏል።
በስብሰባው ላይ የኢጋድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የባለስልጣኑ የጽህፈት ቤት ሠራተኞች፣ የኢጋድ አባል አገራት የጤና ፋይናነስ ሚኒስትር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በአባል አገራቱ ስር የሚገኙ የቁጥጥር፣ የግዢና ደረጃዎች ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።
የአፍሪካ የሕክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ስርአት በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ ስትራይቭ ማሲዪዋ፣ በአፍሪካ በማህበራዊ ጉዳዮች ለሚሰሩ ጀማሪ የቢዝነስ ተቋማት የቴክኖሎጂና የካፒታል ድጋፍ የሚያደርገው ጃኖጎ ተቋም፣ የአፍሪካ ወጪና ገቢ ባንክ (አፍሪኤግዚም ባንክ) እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተዘጋጀ ነው።
በግዢ ስርአቱ አማካኝነት የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ዲጂታል በሆነ መንገድ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ከሚገኙና የብቃት ማረጋገጫ ከተሰጣቸው የሕክምና ቁሳቁስ አምራቾች የኮቪድ-19 መከላከያ የሕክምና ቁሶችን መግዛት ይችላሉ።
የተዘጋጀው የግዢ ስርአት አደረጃጀት አገራት ግልጽና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲገዙ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።
የአፍሪካ ወጪና ገቢ ባንክ ለህክምና ቁሳቁሶች የሚያስፈልገውን ክፍያ የሚያመቻች ሲሆን የአፍሪካ አየር መንገዶች ዓለም አቀፍ የጭነት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁሳቁሱን ለአገራቱ ያደርሳሉ።
የአፍሪካ የሕክምና አቅርቦቶች የዲጂታል ግዢ ስርአት ፈቃድ ለመስጠት በተቀረው ዓለም የሚገኙ አገራትና ተቋማት ጥያቄ እየቀረቡ መሆኑን ከአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።