ቀጥታ፡

ጉባኤው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ ለማምጣት እየሠራ ነው--የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ ነሐሴ 10/1912 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘርን፣ እምነትንና ማንነትን ላይ ያተኮሩ የሚመስሉ ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማምጣት ከመንግሥት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።

ጉባኤው በቅርቡ በሻሸመኔና አካባቢው በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች በተከሰቱ ረብሽ  በጠፋው የሰው ሕይወትና በወደመው ንብረት ምክንያት የተፈጠረው አለመረጋጋት ወደ ቀድሞው ሠላም እንዲመለሥ በኅብረተሰብ መካከል እርቀ ሠላም እንዲሰፍን ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁንም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎች ዘርን፣ሃይማኖትንና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የሚመሥሉና የሰው ሕይወት የሚቀጥፉ፤ ንብረት የሚያወድሙ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው።

በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ረብሽ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱና  ንብረት ማውደሙ  አንዱ ማሳያ ነው።

ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ: የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ናቸው፤ የሃይማኖት ተቋማቱ ጉባኤ በሀገሪቱ ተጠብቆ የቆየው የመተባበርና የመከባበር እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም በቅርቡ በሻሸመኔና አካባቢው ተከስቶ በነበረው የሰው ሕይወትና ንብረት ያወደመው ረብሽ በንፅሃን የአካባቢው ነዋሪ ላይ የጣለውን መጥፎ ጠባሳ በማክሰም ዘላቂ ሠላም በማስፈን  የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን ጠቅላይ ጽሐፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።

በጥቃቶቹ ላይ የየእምነት ተቋማቱ ተከታዮች ተሳትፈዋል ብሎ ጉባኤው እንደማያምን የጠቆሙት ሊቀ ትጉሃን ታጋይ፤ ከ98 ከመቶ በላይ የሚሆነው የእምነቱ ተከታይ ጉዳቱ እንዳይስፋፋ ሲከላከልና የጥቃቱ ሰለባ ሲሆን እንደነበረም በቦታው በመገኘት ማረጋገጥ ተችሏል።

እንዲህ ዓይነቶቹ መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ መንግሥት የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ማሳሰቡን ጠቅላይ ጽሐፊው ተናግረዋል።

“መንግሥት የመንግሥትን ሚና እንዲጫወት እንደ እምነት ተቋማት እያሳሰብን ነው፤ በተለይ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ሰፊ ሥራ እንዲሠራ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማትም ከምንግዜውም በላይ በጋራ እሴቶቻቸው ላይ ጠንክረው ተከታዮቻቸውን ማስተማር እንደሚገባቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ጽሐፊው፤ በተለይ አብሮነታቸው ላይ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተለይ በ12ኛው ጠቅላላ ጉባኤው ላይ በወሰነው መሠረት በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን፣ በሃይማኖቶች መካከል ግጭት እንዳይከሰትና መከባበር እንዲኖር እንዲሁም ዘላቂ ሠላም በሀገሪቱ እንዲሰፍን በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማምጣት በጀት መድቦ እየሠራ መሆኑንም ሊቀ ትጉሃን አስረድተዋል።

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ በሻሸመኔና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት በሰው ሕይወት ላይ ሞትና በንብተረት ላይ ጉዳት ማድረሱን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም