በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ህገ ወጥ የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር ዋለ

66

ጎንደር፣  ነሐሴ 9/2012(ኢዜአ) ንግድ ፈቃድ በሌለው ህገ-ወጥ ነጋዴ ሲዘዋወር የተገኘ ከ6 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር መዋሉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የምግብ ዘይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው በዞኑ ታች አርማጭሆ ወረዳ በኩል ወደ ሁመራና ዳንሻ ከተሞች በድብቅ በተሽከርካሪ በማጓጓዝ ለማስወጣት ሲሞከር ነው፡፡

ህገ-ወጥ የምግብ ዘይቱ የተገኘው  ትናንት ረፋድ ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-  29155 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በድበቅ ተጭኖ ሊወጣ ሲል በሳንጃ ከተማ የፍተሻ ኬላ በተደረገ ቁጥጥር መሆኑን የመምሪው ኃላፊ አቶ አይቸው ታረቀኝ ዛሬ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ያለንግድ ፈቃድ የምግብ ዘይቱን በድብቅ ለማሰወጣት የሞከረው ግለሰብ በጸጥታ ኃይል መያዙንም ጠቁመዋል።

የምግብ ዘይቱ በገበያ ዋጋ ህጋዊ የንግድ ፈቃድ ላላቸው የአካባቢው ነጋዴዎች ተሸጦ ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

በሌላም በኩል ህጋዊ የንግድ ፈቃድ በሌለው ግለሰብ 760 ኩንታል ሲሚንቶ በሁመራ በኩል ወደ ጎንደር ሲገባ በፍተሻ ኬላ ላይ በተደረገ ቁጥጥር መገኘቱንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም