በጎንደር ከተማ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

93
ጎንደር ሀምሌ 5/2010 በጎንደር ከተማ ማራኪ ክፍለ ከተማ ትናንት እኩለ ሌሊት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በማራኪ ክፍለ ከተማ የሶስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ስማቸው ደምሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም 16 የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ተቃጥለዋል፡፡ የእሳት ቃጠሎ ምክንያቱ በአንድ ግለሰብ ሱቅ የኤሌክትሪክ መስመር የፈጠረው  አደጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከተማው የእሳት አደጋና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለሶስት ሰዓታት ባደረጉት ርብርብ ቃጠሎው ወደ ሌላ አካባቢ ተዛምቶ ጉዳት ሳያደርስ  መቆጣጠር ተችሏል፡፡ የንግድ ሱቆቹ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የተሰሩ በመሆናቸው ለቃጠሎው መባባስ ምክንያት መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኢንስፔክተሩ በቃጠሎው የወደመው ንብረት ለጊዜው ግምቱ አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ለእሳት አደጋ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድሞ በመገንዘብ ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላፈዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም