ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ ሳኒታይዘርና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በስፋት ማምረት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 9/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ሳኒታይዘርና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በስፋት ማምረት ጀመረ።

ፋብሪካው ሳኒታይዘርና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በስፋት ማምረት መጀመሩን የተለያዩ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ይፋ አድርጓል።  

የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር መሃመድ ኑሪ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፋብሪካው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ነው።

ኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከሦስት ቀናት በኋላ ሳኒታይዘር አምርቶ ማከፋፈል መጀመሩን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 10 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር እያመረተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚያስፈልጉ ሌሎች ግብዓቶች መካከልም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ፋብሪካው በቅርቡ ማመምረት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለዚህም ፋብሪካው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን የሚያመርቱ መሳሪያዎችን ከውጭ ማስገባቱንና በቀን 100 ሺህ ጭንብሎችን የማምረት አቅም መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው የሚያመርታቸው ሳኒታይዘሮችና ጭንብሎች የሚፈለገውን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያሟሉ መሆኑንም ዶክተር መሃመድ ገልጸዋል።

ፋብሪካው ምርቶቹን በስፋት ማምረቱ አገሪቱ የፊት ጭንብል ለመግዛት የምታወጣውን ወጪ በመቀነስ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

በዛሬው ዕለትም ፋብሪካው 100 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ለግሷል።  

"ፋብሪካው ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ሌሎች ተጓዳኝ ግብዓቶችን በማምረት እገዛ ማድረጉን ይቀጥላል" ሲሉም ገልጸዋል።

"ፋብሪካው ሳኒታይዘርና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማምረቱ ትልቅ እምርታ ነው" ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደጀኔ ዱጉማ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን ተከትሎ ወደኢትዮጵያ የሚገቡት ጭንብሎች በቁጥር አነስተኛ መሆናቸው የአቅርቦት ማነስ ችግር አስከትሏል።

ፋብሪካው ይህንን ክፍተት በመሙላት በኩል ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገለጸው፣ በተለይ የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከል እያደረጉት ላለው ጥረት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስትም ለፋብሪካው የሚያደርገወን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ዶክተር ደጀኔ፣ ኅብረተሰቡም የአፍና አፍንጫ ጭንብል በአግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል።

ህብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች እንዲሁም ሳኒታይዘር ያላቸውን ጠቀሜታ ችላ ሳይል በአግባቡ በመጠቀም የቫይረሱን ስርጭት መከላከል እንዳለበት ገልጸዋል። 

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፤ "ፋብሪካው የተጣለበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ነው" ብለዋል።

በተለይም እነዚህ የመከላከያ ቁሶች በአገር ውስጥ መመረታቸው ምርቶቹን ከውጭ ለመግዛት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

ፋብሪካው ያለውን ሙሉ አቅም አሟጦ በመጠቀም የአፍሪካን ገበያ ለመቆጣጠር መስራት እንዳለበትም መለዕክት አስተላልፈዋል።

"ፋብሪካው ከአፍሪካ ሦስት ቀደምት የመድኃኒት ፋብሪካዎች አንዱ ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት እያደረገ ያለው ትግል የሚበረታታ ነው" ሲሉም አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም