የልማት ፕሮጀክቱ ጀምረን መጨረስ እንደምንችል የተገነዘብንበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ፕሮጀክቱ ጀምረን መጨረስ እንደምንችል የተገነዘብንበት ነው
አዲስ አበባ ነሀሴ 9/2012 (ኢዜአ) ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት የማይሳኩ የሚመስሉ የልማት ውጥኖችን በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻል መገንዘባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ "የኢትዮጵያ ልክ ከግቢ እስከ ሀገር" በሚል ርዕስ ተዘጋቶ ትላንት ምሽት ለተመልካች ከቀረበው ዘጋቢ ፊልም በርካታ ቁምነገሮችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ለኢዜአ አስተያየቱን የሰጠው አቶ ወንድወሰን አርጋው እንደገለጸው ̎ ከዘጋቢ ፊልሙ ሀገራዊ ግዙፍ የልማት ውጥኖችን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ እንደሚቻል ተገንዝቤበታለሁ" ብለዋል።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይሰራሉ ተብሎ የማይታሰቡ ስራዎች በተግባር ተሰርተው ተመልክቻለሁም ነው ያለው ።
ይህም ያለንን አቅም አስተባብሮ መጠቀም ከተቻለ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከፍታ ማማ ማድረስ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ወንድወሰን ̎ አቅሜ የፈቀደውን በማድረግ መንግስት በሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ ሁሉ መተባበር እንዳለብኝ ተነሳሽነት አሳድሮብኛል ̎ሲሉም አክለዋል።
የሸገር ፕሮጀክት ሀገር ውስጥ መሆኑን እስክጠራጠር ድረስ አስደንቆኛል ያሉት ደግሞ አቶ ከይሩ አህመድ ናቸው፣ ያለንን ሃብት በአግባቡ ከተጠቀምን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች መትረፍ እንደምንችል ማሳያ ነውም ብለዋል ።
ሰላም ከሰፈነና ህዝብ ከተባበረ ወደ ብልጽግና የሚደረግን ጉዞ ማንም እንደማያደናቅፈው ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የተላለፈው ፕሮግራም የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔ እንዲሁም ያላትን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብት ቁልጭ አድርጎ ያመላከተ እንደነበር ገልጸዋል።
ሀገራችን የባለብዙ ጸጋ ባለቤት በመሆኗ ከኛ የሚጠበቀው ጠንክሮና ተባብሮ መስራት ብቻ ነው" የሚሉን የአዲስ አበባው ነዋሪ አቶ በሃይሉ መኮንን ናቸው።
በሁለት አመት ውስጥ ይህን ያክል ስራ መሰራቱ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚቻል አመላካች ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በተለይ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የአስተሳሰብ አንድነት ያስፈልጋል ፣በአስተሳሰብ ከተለወጥንና ለአንድ አላማ በጋራ ከሰራን እንደ ሀገርም እንደ ህዝብም ሃያል የማንሆንበት ምንም አይነት ምክኒያት አለመኖሩን ከዘጋቢ ፊልሙ መገንዘብ ችያለሁ ብለዋል አቶ መኮንን።