ማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ኮሮናቫይረስ በክልሎች ያለበትን የሥርጭት መጠን ለማወቅ ይረዳል---ጤና ሚኒስቴር

53

አዲስ አበባ ነሐሴ 9/2012 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራና የግንዛቤ ዘመቻ ኮሮናቫይረስ በክልሎች ያለበትን የሥርጭት መጠን ለማወቅና ለአገራዊ ውሳኔዎች የሚረዳ መረጃ ለማግኘት እንደሚያስችል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን በላይ መመርመሪያ ኪቶች፣ ከ70 ሺህ በላይ አልጋዎችና ሌሎች ቁሶች መዘጋጀታቸውም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የሚያዘው ሰው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የቫይረሱ ሥርጭት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራ ዘመቻ በቅርቡ መጀመሩ ይታወቃል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በይፋ ባስጀመሩት በእዚህ የምርመራ ዘመቻ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ከ200 ሺሀ በላይ ሰዎችን ለመመርመር ታቅዷል።

የጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ጄነራል ዳይሬክተርና ኮቪድ-19ን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ያዕቆብ ሰማን እንደሉት በክልሎች የቫይረሱ ሥርጭት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ በቂ መረጃ የለም።

"በሁሉም ክልሎች በሚደረግው የምርመራ ዘመቻም የቫይረሱን የሥርጭት መጠን ለማወቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል።

አቶ ያዕቆብ እንዳሉት እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ አንዳንድ ክልሎች የምርመራ አቅማቸው በጨመረ ቁጥር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችም በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ታይቷል።

እስካሁን በአገሪቱ ምርመራ ከተደረገላቸው ከ560 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ ሥርጭት ጎልቶ በሚገኝባት አዲስ አበባ ከተማ የተገኙ ናቸው።

አሀዙ በክልሎች የቫይረሱ የሥርጭት መጠን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ከመጠቆም ውጭ በምርመራ የተረጋገጠ መረጃ አለመኖሩንም ነው አቶ ያዕቆብ ያስረዱት።

ይህ ደግሞ የኮሮናቫይረስ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተሰራጭቶ ለከፍተኛ ቀውስ እንደሚዳርግና ቀድሞ መከላከል ባለመቻል የሚደርሰውን ጉዳት በቀላሉ ለመቋቋም እንደሚያስቸግር አስረድተዋል።

አቶ ያዕቆብ እንዳሉት አሁን ባለው ሁኔታ ቫይረሱ በሁሉም ክልሎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ስለመሰራጨቱ ማሣያዎች ተገኝተዋል።

በቅርቡ የተጀመረው የማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራና የግንዛቤ ዘመቻ ሁሉንም ክልሎች ያካተተና በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎች የሚመረመሩበት ነው።

"ይህም የቫይረሱ ሥርጭት በክልሎች በምን ደረጃ እንዳለ መንግሥት በሚገባ አውቆ ለውሳኔዎች ምን ዓይነት አቅጣጫን መከተል እንዳለበት የሚረዳ መረጃን ያስገኛል" ብለዋል።

በተለይ በክልሎች በሰዎች መዘናጋትና በማኅበራዊ ጥግግቶሽ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሳይመረመሩ በኮሮናቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን አቶ ያዕቆብ አመልክተዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ ማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራና የግንዛቤ ዘመቻው በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክልሎች ከተጀመረ ካለፈው ሣምንት ወዲህ ከሚመረመረው ሰው ከ700 በመቶ በላይ የሚሆነው በቫይረሱ መያዙን መረጃዎች እያሳዩ ነው።

መንግሥት ለምርመራው ከአንድ ሚሊዮን በላይ መመርመሪያ ኪቶችን፣ ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ወረዳዎች ከ70 ሺህ በላይ አልጋዎችንና ሌሎች ቁሶችን ዝግጁ ማድረጉንም አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል።

አቶ ያዕቆብ እንዳሉት ለሁለት ሣምንት እየተካሄደ ባለው በእዚህ ዘመቻ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ ይችላል ተብሎ ግምት ተቀምጧል።

በመላ አገሪቱ እየተካሄደ ላለው የምርመራ ዘመቻ ከተዘጋጁት አልጋዎች ከ50 ሺህ በላይ በለይቶ ማቆያ ለሚገቡ ሕሙማን የሚያገለግሉ ሲሆን ቀሪው 20 ሺህ አልጋ ለማከሚያነት እንደሚውሉ አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል።

ለንቅናቄው መሳካት ሁሉም የክልል አመራሮች፣ የሕክምና ባለሙዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም