ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ግብጽ በአባይ ውሃ መግባባት ያልቻሉት ባላቸው መሰረታዊ የዲፕሎማሲ ልዩነቶች ነው

አዲስ አበባ  ነሀሴ 9/2012  (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ግብጽ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ መግባባት ያልቻሉት ባላቸው መሰረታዊ የዲፕሎማሲ ልዩነቶች መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያን የሰላም ህልውና ማረጋገጥ ሳይቻል ትላልቅ የልማት ፕሮጀክት እውን ለማድረግ መሞከር ፈታኝ መሆኑንም አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረች ጀምሮ ከታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችና ድርድሮችን እያካሄደች መሆኑ ይታወቃል።

ይሁንና ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከባለሙያዎቻቸው እስከ መሪዎቻቸው ድረስ ያደረጓቸው ውይይቶች የተጨበጠ ውጤት ማምጣት አልቻሉም።

ግብጽ በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በየጊዜው የምታመጣቸው እቅዶች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማያስጠብቁና ሉዓላዊነትን የሚዳፈሩ በመሆናቸው ውድቅ ሲደረጉ ቆይተዋል። 

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር  እንዳለ ንጉሴ በተለያዩ አገሮች በቅኝ የተገዛችው ግብጽ የምታራምደው ዲፕሎማሲ ተለዋዋጭና በማታለል ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነጻና መርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ ከምትከተለው ኢትዮጵያ እንዲለይ እንዳደረገው ገልጸዋል።

የግብጽ የመንግስት መዋቅርም ሆነ ከአገሮች ጋር የሚደረግ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በፍላጎታቸው ላይ ብቻ የተመሰረተ የሌሎችን ጥቅም የማያስጠብቅ መሆኑን ነው የሚያነሱት። 

''ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ውሃ አሞላል ላይ እስካሁን ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ያለውጤት የመጠናቀቁ ምስጢር ግብጽ ናት'' ያሉት አቶ እንዳለ፤ ግብጽ የውስጥ የፖለቲካ ችግሯን የምታረጋጋው የአባይን ውሃ አጀንዳ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የታችኛው ተፋስስ ሀገራት የኢትዮጵያን አቋም እንዲረዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርና በሀገር ውስጥ የሚስተዋለውን አለመግባባት በንግግር በመፍታት ለሀገር  እድገት በጋራ መስራት ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የምክክር፣ የጥናትና የትብብር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብደታ ድርብሣ ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ጌታቸው መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምትከተለው የዲፕሎማሲ መርህ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህንን መርህ አገሮቹ እንዲገነዘቡት በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት አጠናክራ ለማስቀጠልና ልማቷን ለማፋጠን ውስጣዊ ሰላሟን ማስጠበቅ አለባት።

የትኛውም የልማት ፕሮጀክት የአገሪቷ የሰላም ህልውና ካልተረጋገጠ እውን ሊሆን እንደማይችልም አጽንኦት ሰጥተውታል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ድርድር እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።


ሰሞኑን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ሶስቱ አገሮች ለሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም በሱዳን ጥያቄ ድርድሩ በድጋሚ እንዲራዘም ተወስኗል።


የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ ኢትዮጵያ የራሷን ሰነድ ከሁለት ሳምንት በፊት ያቀረበች ሲሆን፣ በዚህም ግብፅና ሱዳን ሰነዱን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ድርድሩ እንዲራዘም በማድረግ ላይ ናቸው። 


አገሮቹ ድርድሩን በመቀጠል የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ቢሮ ስብሰባ በተካሄደ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የመካከለኛና የመጨረሻ ሪፖርት ለኅብረቱ ሊቀመንበር ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይጠበቅ ነበር። 

ድርድሩ በመጪው ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም