ቀጥታ፡

የክልሉ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 8/2012 ( ኢዜአ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር ዛሬ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 3 ሺህ ኩንታል የምግብ ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ፡፡

የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር ዛሬ በድጋፉ ርክክብ ሥነ ሥርዓት  ላይ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫውም የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት በደምና በአጥንት የተሳሰረና ታሪካዊ ግንኙነትም እንዳለው  ተገልጿል፡፡

የህዝቦቹ መደጋገፍና አብሮ የመቆም ታሪክ የነበረና ለወደፊትም እንደሚዘልቅ ተጠቁሟል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉትም አሁን የመጣው ለውጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ተጠቃሚ ያደረገ ቢሆንም ለውጡ እንዲመጣ ግን የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ጨቋኝ ሥርዓት ህዝቦቹ በኦኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎችም ተጠቃሚ እንዳልነበሩም ጠቅሰዋል፡፡

ሁለቱ ህዝቦች በጋራ በሰሩት አኩሪ ስራም ጨቋኙን ሥርዓት ዳግም ላይመለስ ሸኝተው ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ የሆኑበትን ለውጥ ማምጣታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በኦሮሚያ ክልልም ይሁን በሌሎች ቦታዎች ጥፋት በማድረስና ህዝቦችን በመጉዳት አገርን ማፍረስ እንደማይቻል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የክልሎቹ ህዝቦች ለጥፋት የተሰማሩ ኃይሎች በአብሮነትና በጋራ በመቆም እንደሚታገሏቸው ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን ህዝቦች በአብሮነት የመልማትና ማገድ ዕቅድም ማንኛውም አካል ወደኋላ መመለስ እንደማይችልም አቶ ተመስገን  አስረድተዋል፡፡

ክልሉ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ተጎጂዎቹ ወደ ነበሩበት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እስኪመለሱ ድረስም ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ  አረጋግጠዋል፡፡

ለወደፊትም ክልሎቹ በሁሉም ዘርፎች በትብብር  እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የአማራ ክልል ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የኦሮሞና አማራ በደስታም በሀዘንም ጊዜ አብሮነታቸውን ያረጋገጡ ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ህዝቦች በአንድ ላይ ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋቸው በብቃት አብረው ያለፉ ናቸው ሲሉም  ተናግረዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ቀደምም ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ጎን መቆሙንና ለውጡ እንዲመጣም መስዋዕትነት መክፈላቸውንም አስታውሰዋል፡፡ 

የኦሮሞና አማራ ህዝቦች ትናንትም ዛሬም ለወደፊትም ተዋደውና ተከባብረው አብረው የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም