ለዶክተር ፍስሃዬ አለምሰገድ የመታሰቢያ ስነ ስርአት ተካሄደ

75

አክሱም  ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) ከዶክተር ፍስሃዬ አለምሰገድ ቅንነት እና ታማኝነትን መማር ይገባል ሲሉ የአክሱም ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

የዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ ''በሙያህ እስከ መስዋእትነት ለከፈልከው ህይወት ታላቅ ክብር አለን'' በሚል መሪ ቃል በኮሌጁ ግቢ የመታሰቢያ ስነ ስርአት ዛሬ ተካሄዷል።

የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደጀን ገብረመስቀል በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ህብረተሰብን በታማኝነት ማገልገል እና በሙያ መስዋእትነት መክፈል ከዶክተር ፍስሃዬ ልንማር ይገባል።

"ዶክተር ፍስሃዬ በሆስፒታሉ ቆይታው በትምህርት እና በሙያው ያካበተውን ልምድ እና እውቀት ለጤና ባለሙያዎች አካፍሏል፣በጤና ዘርፍ ለሪፈራል ሆስፒታሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል" ያሉት ዳይሬክተሩ እስከ ህልፈታቸው ድረስም ቫይረሱን በመከላከልና ህሙማንን በመንከባከብ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸዋል።

በሪፈራል ሆስፒታሉ እና በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አስተዳደር ሁሉም ወረዳዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ፈጣን ግብረ-መልስ ክፍል አስተባባሪ በመሆንም አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸማቸውንም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ መብራህቱ አባይ በበኩላቸው በአካዳሚክ ጉዳዮች ተማሪዎች እና መምህራን ከዶክተር አለምሰገድ ብዙ ቁም ነገር እንደተማሩ እና ሁሌም እንደሚታወሱ ተናግረዋል።

"ለህዝብ ሲል ህይወቱን ከፍሎ፣በታማኝነት እና በቅንነት ህዝብን በሙያ ማገልገል ክብር መሆኑን አስተምሮናል'' ብለዋል።

ዶክተር ፍስሃዬ የኮሮና ቫይረስ በመከላከል ዙሪያ የማይረሳ ሙያዊ ድጋፍ እድርጓል ያሉት ደግሞ የአክሱም ከተማ የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ሺፈራው ናቸው።

"በሙያ ህብረተሰብን በቅንነት እና በታማኝንት ማገልገል ከእሳቸው መማር ይገባል" ብለዋል።

በጤና ዘርፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር እንደነበሩ የሚነገርላቸው ዶከተር ፍስሃዬ ከ50 በላይ የተለያዩ አለም አቀፍ ጥናቶች እና የምርምር ውጤቶች በታወቁ ጆርናሎች ማሳተማቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም