በተከዜ ወንዝ ላይ የተሰራ ድልድይ በጎርፍ በመደርመሱ የእንቅስቃሴ ችግር መፍጠሩ ተገለጸ

58

ሰቆጣ፣ነሃሴ 8/2012(ኢዜአ)  በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በተከዜ ወንዝ ላይ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ድልድይ በጎርፍ መደርመሱ የእንቅስቃሴ ችግር ማስከተሉን በዞኑ የዝቋላ ወረዳ መንገድ እና ትራንስፖርት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ፋንታየ አብርሃ ለኢዜአ እንደገለፁት የተደረመሰው የተከዜ ወንዝ ድልድይ የዝቋላ እና የሰሃላ ወረዳዎችን በማገናኘት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ነው።

በ2000 ዓ.ም በፌደራሉ መንግስት የተገነባው ይሔ ድልድይ ለአስር አመታት እንደሚያገለግል ታሳቢ የተደረገ እንደነበረም ተናግረዋል።

ድልድዩ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በጎርፍ እና በደለል ምክንያት ለጉዳት ሲዳረግ እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው ባለፈው አመት ከ57 በላይ የድልድዩ ማገናኛ ብሎኖች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ወልቀው እንደገና መጠገናቸውንም አውስተዋል።

ዘንድሮ በተባባሰው የክረምት ዝናብ ነሃሴ 6/2012 ዓ.ም ሌሊት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የድልድዩ ግማሹ ክፍል መደርመሱን አስረድተዋል።

"በዚህ ምክንያትም ከሰሃላ ወረዳ ወደ ከዝቋላና የዞኑ ከተማ ወደ ሆነችው ሰቆጣ የሚደረገው የትራንስፖርት ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል" ብለዋል።

የደረሰውን ችግር ለማስቀረት ወይም ለመከላከል በዞኑ ደረጃ የተደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ ከክልሉና ከፌዴራል መንግስት ተቋማት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዝቋላ ወረዳ የተከዜ ወንዝ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ አየለ ደስታ እንደተናገሩት ድልድዩ ከተገነባ ወዲህ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ እፎይታን ፈጥሮላቸው ቆይቷል።

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በጎርፍ አደጋ እየተጎዳ እና በውሃ እየተዋጠ በመምጣቱ ያሳለፉት የስቃይ ዘመናት እየተመለሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተከዜ ድልድይ ላይ እያጋጠመ ያለው ችግር እንዲፈታ የአካባቢው ህብረተሰብ በተደጋጋሚ እያቀረበ ያለው ጥያቄ የሚፈለገውን ያክል ፈጣን ምላሽ እንዳላገኘም አስረድተዋል።

ድልድዩ ሁለቱን ወረዳዎች ከማስተሳሰር ባለፈ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደርን ከሰሜን ጎንደር የሚያገናኝ መሆኑም ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም