በባህር ዳር ከተማ ጭንብል ሳይለብሱ የተገኙ 100 አሽከርካሪዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ ጭንብል ሳይለብሱ የተገኙ 100 አሽከርካሪዎች ተቀጡ
ባህርዳር ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) በባህርዳር ከተማ ኮሮናን ለመከላከል የተላለፈን መመሪያ ጥሰው ጭንብል ሳይለብሱ የተገኙ 100 አሽከርካ ሪዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የመምሪያው የህብረተሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል የስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው አየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ጭምብል የመልበስ አስገዳጅ መመሪያ ተላልፏል።
ህብረተሰቡ ጭንብል ሳይለብስ እንዳይንቀሳቀስ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች፣ በገበያ ቦታ፣ በታክሲ መነሻና መድረሻ ፌርማታዎች ህግ የማስከበር ስራ በፀጥታ አካላት እየተከናወነ ይገኛል።
በተደረገ ህግ የማስከበር ስራም ጭንብል ሳይለብሱ ሲያሽከረክሩ የተገኙ 100 አሽከርካሪዎች ከ118 ሺህ ብር በላይ መቀጣታቸውን ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው አስታውቀዋል።
በዚህም መሻሻል ታይተው የነበሩ ቢሆንም አሁንም አብዛኛው ህብረተሰብ ጭንብል ሳይለብስ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በአግባቡ እንዲጠቀም የፀጥታ ኃይሉ በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ በሽታውን በመከላከል በኩል እያሳየ ያለው መዘናጋት ዋጋ ስለሚያስከፍለው ህጉን በማክበር ርቀቱን ጠብቆ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ለብሶ እንዲንቀሳቀስ የማስገንዘብ ስራም እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።
አስገዳጅ ህጉ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል ሳያደርጉ እንደማያሽከረክሩ የገለጹት ደግሞ በከተማ የታክሲ አሽከርካሪ አቶ ኃይሌ ምስጋናው ናቸው።
ጭንብል ሳይለብሱ ለመሳፈር የሚመጡ ተገልጋዮችም ስላሉ ህብረተሰቡ በሽታውን እንዲከላከል ግንዛቤውን የማሳደግ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።
የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ስንዱ በላይ በበኩላቸው " በሽታውን ለመከላከል ርቀታችሁን ጠብቁ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ተጠቀሙ ስል ፈጣሪ ነው የሚጠብቀን የሚል ምላሽ ይሰጡኛል " ብለዋል።
ማንኛውም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይለብስ እንዳይንቀሳቀስ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።