በኦሮሚያ ክልል ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች አሉ--የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች አሉ--የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች መኖራቸውን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተከሰተው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ ላይ ፈጣን ምርመራ ማድረግ መጀመሩን በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ከ40 በላይ ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ የምርመራ ቡድኖችን በማሰማራት ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ምስክሮችን እና የመንግስት አካላትን በማነጋገር መረጃ ለማሰባሰብ እና አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ጥረት አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በምርመራው ወቅት የታዩና በአፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያሰባቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስጋቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በይፋ በማሳወቅ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ያስችል ዘንድ አሁንም የጥቃት ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎችን በተመለከተ፣ ሰብዓዊ እርዳታ፣ ድጋፍ እና የተፈናቀሉ ተጎጂዎች ሁኔታ እና የእስረኞች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
አሁንም የጥቃት ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎች በተመለከተ፤ የምርመራ ቡድኖች በተጓዙባቸው በአብዛኛው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የተሻለ መረጋጋት ያለ መሆኑን በመግለጫው ገልጿል።
በአንዳንድ አካባቢዎች በሰዎች ህይወት፣ አካላዊ ደህንነት እና ንብረት ላይ የጥቃት ስጋት እንዳለ ኮሚሽኑ ለመገንዘብ መቻሉን በመግለጫው አመልክቷል።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ተጎጂዎች በተለያዩ ቡድኖች የጥቃት ማስፈራሪያ እና ዛቻዎች እየደረሳቸው እንደሆነ ለኮሚሽኑ ማስረዳታችውን ነው ያስታወቀው።
ችግሮቹ በዶዶላ፣ በሻሻመኔ፣ በባቱ ከተማ እየተስተዋሉ መሆናቸውን አመልክቷል።
በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ለአብነትም (በቡራዩ ከተማ በተለይ ከታ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ እንዲሁም በጉና ወረዳ ነገሌ ከተማ) በመንግስት የፀጥታ አካላት ሳይቀር ሰዎች እየተደበደቡና ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለማወቅ መቻሉን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ሰብዓዊ እርዳታ፣ ድጋፍ እና የተፈናቀሉ ተጎጂዎች ሁኔታ በተመለከተም፤ ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ የተቻለ ቢሆንም ተጎጂዎችን ወደ ነበሩባቸው ቦታዎች ለመመለስ እና መልሶ ለማቋቋም መጠነ ሰፊ ስራ እና ጊዜ የሚያስፈልግ እንደሆነ ኮሚሽኑ መገንዘቡን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ለተጎጂዎች ድጋፍ ማቅረብ እና ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የእስረኞች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የምርመራው ቡድን የደረሰበትንም ገልጿል።
ኮሚሽኑ ምርመራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመገንዘብ የቻለ መሆኑን ነው የጠቀሰው።
እስካሁን በጎበኛቸው የእስር ቦታዎች የሰብዓዊ መብት ችግሮች፣ ለኮቪድ 19 አጋላጭ ሁኔታዎችና ፍርድ ቤት በጊዜ አለማቅረብን የመሳሰሉ ችግሮች መኖራቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።
በተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ ለሌላ ጥቃት እንዳይዳረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡
ስለዚህም የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጥበቃ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚረዳ ቢሆንም መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች አፋጣኝ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበትና በተለይም አሁን ያለንበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የክረምት ወቅት ስለሆነ ተጎጂዎች ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳረጉ ማድረግ እጅግ የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው ሲል አሳስቧል።