የዳያስፖራ ማህበረሰብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ700 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የዳያስፖራ ማህበረሰብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ700 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ በ2012 በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 737 ሺህ 506 ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የዳያስፖራው ማህበረሰብ ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የዳያስፖራው ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ ጊዜያት መቀዛቀዝ እንደነበር አስታውሰው ከለውጡ በኋላ ግን ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ሂደት የነበሩበት ችግሮች ተወግደው በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ በመሆኑ እና የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌቱም መካሄዱ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በዲፕሎማሲው መስክ የተገኘው ስኬትም ይበልጥ ተነሳሽነት እንዲኖር ማድረጉንም አመልክተዋል።
በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመትም የዳያስፖራ ማህበረሰብ 737 ሺህ 506 ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ወይዘሮ ሰላማዊት ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በዳያስፖራው በኩል ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።
የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ በዳያስፖራው በኩል ድጋፍ ለማድረግ ያለው ተነሳሽነት መጨመሩን ተከትሎ የተሻለ ሀብት ለማሰባሰብ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
ኤጀንሲው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ቡድን መዋቀሩንም ገልጸዋል።
ኤጀንሲው ለህዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወኑ ይገኛሉም ብለዋል።
በዚሁ መሰረት የዳያስፖራው ማህበረሰብ ድጋፍ የሚያደርግባቸውን አማራጮች የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ይሄም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ለህዳሴው ግድብ ዳያስፖራው ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብቷን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳት ተግባርም እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የሚታዩ መልካም ጅምሮችና ሚዛናዊ ምልከታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ህዳሴ ግድብ የማስረዳትና የማስገንዘብ ተግባር በተደራጀ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የዳያስፖራው ማህበረሰብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በ2013 ዓ.ም በጀት ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 200 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ745 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 71 ሚሊዮን 431 ሺህ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዳያስፖራው ድርሻ 1 ቢሊዮን 6 ሚሊዮን ብር ነው።