በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ - ኢዜአ አማርኛ
በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት በተመለከተ የአንድ ሳምንት ቦንድ ሽያጭ አዘጋጅቶ ነበር።
የቦንድ ሸያጭ ሳምንቱም "የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የውሃ ሙሌት መጀመር ታላቅ የምስራች ነው፤ ለግድቡ መጠናቀቅ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" በሚል መሪ ሃሳብ ተከናውኗል።
በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከነሀሴ 3 እስከ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው ሸያጭ የአንድ ሚሊዮን 15 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተዋል።
በኩዌት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ እንዳሉት የመጀመሪያው የግድቡ የውሃ ሙሌት የተከናወነው በለውጥ አመራሩ ቁርጠኝነትና በህዝቡ ተሳትፎ ነው።
ይሄውም በኢትዮጵያ የይቻላል መንፈስ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያብብ ያደረገ፤ መጀመር ብቻ ሳይሆን ማጠናቀቅም እንደምንችል ያሳየንበት ተግባር ነው ብለዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለፍጻሜ እስከሚበቃ ድረስ ከህፃን እስከ አዋቂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ለግድቡ መጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመላክታል።
በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በ2012 በጀት ዓመት ብቻ 7 ሚሊዮን 395 ሺህ 500 ብር የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን የተላከው መግለጫ ያሳያል።
በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ቦንድ ለመግዛት ሰሞኑን ቃል መግባታቸው ይታወቃል።