ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ድርድር ኢትዮጵያ በወንዞቿ ላይ የልማት ስራዎችን በቀላሉ ማከናወን እንድትችል መሰረት ጥሎ ማለፍ አለበት

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 8/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ከታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር እያካሄደችው ያለው ድርድር በሌሎች ወንዞቿ ላይ የልማት ስራዎችን በቀላሉ እንድታከናውን የሚያስችል መሰረት ጥሎ ማለፍ እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የግድቡ ግንባታ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የነበረውን የተሳሳተ ምናባዊ ትንተና  እንደቀየረ አንስተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ከጥንት ጀምሮ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አቋም መያዟን ገልጸዋል።

ይሁንና በተለይ የታችኞቹ የወንዙ ተፋሰስ አገሮች ኢትዮጵያ ውድቅ ያደረገቻቸውን  የቅኝ ግዛት ውሎች ጭምር እንድትቀበል የሚያደርጉት ጥረት የአገሪቷን ብሄራዊ ጥቅም የሚገዳደር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

የድርድር ሂደቱ ኢትዮጵያ ወንዞቿን አልምታ መጠቀም በሚያስችላት መልኩ መካሄድ እንዳለበት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ድርድሮች በአባይ ወንዝም ሆነ በሌሎች ወንዞች ላይ ለሚሰሩ  የልማት ስራዎች ጥያቄ በማያስነሳ መልኩ መሰረት ጥለው ማለፍ አለባቸው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

የምክክር፣ የጥናትና የትብብር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብደታ ድርብሣ የአባይ ግድብ በአፍሪካ የ2063 አጀንዳዎች ላይ ከተቀመጡ ጉዳዮች አንዱ መሆኑንና የበርካታ አፍሪካውያንን ህይወት ይቀይራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ከግብጽና ሱዳን ጋር እየተካሄደ ያለው ድርድርም ኢትዮጵያ ለመልማት የምታደርገውን ጥረት በማያደናቅፍ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባው አክለዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማሲ ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር  አቶ እንዳለ ንጉሴ  በበኩላቸው “የግድቡን ግንባታ መጀመር ነበር ከባዱ ያን እርምጃ አልፈነዋል፤ ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበሩት መንግስታት ማድረግ ያልቻሉትን ማድረግ ተችሏል” ብለዋል።

በራስ አቅም ትልቅ ነገር መስራት እንደምንችል የወንዞች፣ የልማት፣ የትምህርትና ሌሎች ስራዎችንም መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪው  አቶ ጌታቸው መኮንን የሶስቱ አገራት ድርድር አድካሚና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎቹ ባደረጉት ትግል ኢትዮጵያ ወደ ምትፈልገው፣ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም መሸጋገሩን አንስተዋል።

እንደ ዶክተር አብደታ ገለጻ፤ ግብጽም ሆነች ሌሎች  የአለም አገሮች ስለ አባይ  ወንዝና  የኢትዮያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተሳሳተ ምናባዊ ትንተና አላቸው።

አገሪቷ በእርስ በርስ ግጭት የተዳከመች በመሆኗ የአባይን ወንዝ ለልማት  የመጠቀም  ዕድል የላትም የሚለው ምናባዊ ትንተና አንዱ መሆኑን ለአብነት ያነሳሉ።

በሌላ መልኩ በአባይ ወንዝ ላይ ትላልቅ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል  የገንዘብ አቅም የሌላትና አለምአቀፍ ተቋማትም ብድር እንደማታገኝ እርግጠኛ ነበሩም ብለዋል።

ይሁንና ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እያከናወነች ያለው የህዳሴ ግድብ ምናባዊ  ትንተናዎችን ውድቅ ያደረገና የአገሪቷን የልማት ፍላጎት በተግባር ያሳየ እንደሆነም  ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ ግድቡን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እያንዳንዱ  ኢትዮጵያዊ  የድርሻውን  እንዲወጣ  ጥሪ አቅርበዋል።

የሚደረገው ድርድርና ውይይት በታችኞቹ ተፋሰስ ብቻ ሳይወሰን ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋርም መካሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እያከናወኑት ያለው ድርድር እስካሁን መቋጫ አላገኘም።

የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ አሁን ላይ 75 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር 4  ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል።

በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት ሙከራ  እንደሚደረግም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም