የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኩላሊት ህሙማን የህክምና ግብአት መግዣ 837 ሺህ ዶላር ፈቀደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኩላሊት ህሙማን የህክምና ግብአት መግዣ 837 ሺህ ዶላር ፈቀደ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኩላሊት ህሙማን ለአንድ ዓመት ኩላሊት እጥበት የቁሳቁስ መግዣ የሚሆን 837 ሺህ ዶላር ፈቀደ።
የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ የኩላሊት እጥበት ለማድረግ የሚያግዙ ግብአቶች እጥረት በማጋጠሙ ህሙማኑ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑ ይነገራል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኩላሊት እጥበት የግብአት መግዣ 837 ሺህ ዶላር መፍቀዱን የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ገልጸዋል።
ባንኩ የፈቀደውን ገንዘብ ድርጅቱ መረከቡንም ተናግረዋል።
የተፈቀደው ገንዘብ ለአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት ግብአት መግዣ የሚያገለግል መሆኑንም ገልጸዋል።
የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በኋላ ዘሉሲና ላዳ ታክሲዎች ለታማሚዎች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ታክሲዎቹ በቀጣይም ነፃ አገልግሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል።
የኩላሊት ህሞማንም የትራንስፖርት አገልግሎት ሲፈልጉ በ6474 ላይ በመደወል መጠቀም ይችላሉም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ 10 ሚሊዮን ብር በመመደብ በዳግማዊ ሚኒሊክና ዘውዲቱ ሆስፒታል እንዲሁም በቅዱስ ጳውሎስ እጥበት ሲያደርጉ ለነበሩ ህሙማን ለአንድ አመት ነጻ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ ይታወሳል።
የከተማዋን ጤና ቢሮና ከተማ አስተዳደሩን እንዲሁም ህመምተኞችን እየደገፉ ላሉ ቢጂ አይ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስራ አስኪያጁ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌሎች ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ እና የእነዚህን ህሙማን ተስፋቸዉን ማለምለም እንዳለባቸዉገልጸው፤ በቀጣይም ማህበረሰቡ በ8582A አጭር የፅሁፍ መልዕክት በመላክ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።