ቀጥታ፡

የኮሮናቫይረስ ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ እንዲሳካ ድጋፋችንን እናጠናክራለን--- የጤና ሙያ ማህበራት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7/2012 (ኢዜአ) የጤና ሙያ ማህበራት አገርአቀፉ የኮሮናቫይረስ ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ እንዲሳካ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ።

ማህበራቱ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ቢመጣም በህብረተሰቡ እየተስተዋለ ያለው የመከላከያ መንገዶች አተገባበር እየቀነሰና ተከታታይነት እያጣ መሆኑ ዋጋ ስለሚያስከፍል ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብር ጠይቀዋል።

ቁጥራቸው 11 የሆኑ የጤና ሙያ ማህበራት የቫይረሱ ስርጭት ከቀን ወደቀን እያሻቀበ መሄዱን ተከትሎ ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ባሏቸው ተግባራት ላይ ዛሬ በቅንጅት መግለጫ ሰጥተዋል።   

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን "ለተጀመረው አገራዊ ዘመቻ መሳካት የሙያ ማህበራት የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው" ብለዋል።

በምርመራው ውጤት መሰረት መከናወን የሚገባቸው የመከላከልና የሕክምና ተግባራት በብቃት እንዲተገበሩም ነው ያሳሰቡት።

በዘመቻው በሚደረግ ምርመራ የኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ የተወሰነ ምልክት የሚያሳዩና ምንም የበሽታ ምልክት የሌላቸው የኀብረተሰበ ክፍሎች በቤታቸው ተወስነው ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚደረገው አማራጭ በጥንቃቄና በስርዓት እንዲተገበርም መክረዋል።

በቤታቸው በሚቆዩበት ወቅት ተገቢ መረጃና የጤና ክትትል የሚያገኙበት መንገድ መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የጤና አመራሮችና በየክልሉ የሚገኙ አባሎቻቸው በዘመቻው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ በማህበሩ በኩል ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በኮቪድ-19 የሚያዙ ጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ለጤና ባለሙያዎች የሚቀርበው የግል ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሻሻልና ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን ከዚህ ቀደም መጠየቁን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የጤናው ዘርፍ አመራሮች ችግሩን ለመቅረፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ነው ዶክተር አለማየሁ ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አመዘነ ታደሰ በበኩላቸው ማህበራቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል።

የግል ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት በመላው ዓለም የተከሰተ ችግር መሆኑን አንስተው በተለይ በጤና ተቋማት ላሉ ኢንተርንና ሬዚደንት ኃኪሞች በአግባቡ መዳረስ እንዳለበት አስረድተዋል።

በዓለም ላይ ለኮሮናቫይረስ የሚመረት ክትባት ውጤታማነቱና ተገቢነቱ ቢረጋገጥ እንኳ ወደታዳጊ አገራት ለመድረስ ጊዜ ስለሚፈጅ ኀብረተሰቡ የጥንቃቄና የመከላከያ መንገዶችን መከተል አሁንም እንደአማራጭ መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም