በአፋር ለኮሮና መከላከል ስራ 74 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ለኮሮና መከላከል ስራ 74 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ሰመራ፣ ነሐሴ 6 / 2012 (ኢዜአ) በአፋር ከልል ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራ የሚያግዝ ከ74 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እንደገለጹት በክልል ደረጃ ግብረ ኃይል በማቋቋምና የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር የኮሮና መከላከልና ቁጥጥር ስራ እየተካሄደ ነው።
በዚህም እስካሁን ከባለሀብቱ እሰከ አርብቶ አደሩ ያለውን ማህበረሰብ በማስተባበር 74 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ገንዘብና ቁሳቁስ መሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው ድጋፍ ውስጥ 16 ሚሊዮን ብሩ በጥሬ ገንዘብና ቀሪው በቁሳቁስ የተገኘ ነው።
በተጓዳኝም ኮሮናን ለመከላከል የወጣን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈው የተገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከሁለት ሚሊዮን 700 ሺ ብር በላይ እንዲቀጡ መደረጉን አመልክተዋል።
ከተቀጡትም መካከል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችና ከተፈቀደላቸው የሰው መጠን በላይ ህዝብ አሳፍረው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።
በገንዘብ የተቀጡት 581 ነጋዴዎች፣984 መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻና 738 ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች እንደሆኑም አመላክተዋል።
በተጨማሪም 1 ሺህ 279 ነጋዴዎች በእስራት፣ 385 ንግድ ፍቃዳቸው የተሰረዘና 6 ሺህ 475 ነጋዴዎች በማስጠንቀቂያ መቀጣታቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ አብራርተዋል።
የአፋር ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ በክልሉ ዋና ኦዲተርና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እየተወያየ ነው።