በኮቪድ-19 ዙሪያ የሚስተዋለው መዘናጋት የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ጫና ውስጥ ሊከተው ይችላል... የጤና ሚኒስቴር

63

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2012(ኢዜአ) በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት የኮቪድ 19 ስርጭት እንዲባባስ ከማድረግ ባሻገር የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ጫና ውስጥ ሊከተው እንደሚችል የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት እየተሻሻለና ለውጥ እያሳየ ቢሆንም በርካታ ቀሪ ተግባራት አሉት።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት መጠን እየጨመረ ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት ደግሞ አገሪቱ ካላት የጤና ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ።

አገሪቷ ያላት የመመርመር አቅም ቢጨምርም በቫይረሱ እየተያዘ ያለው ሰው ደግሞ በዚያው ልክ መጨመሩ ሥርዓቱን ጫና ውስጥ ከትቶታል ብለዋል።

ሚሊኒዬም፣ኤካ ኮተቤና ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዙ ታካሚዎችን በማስተናገዳቸው እየተጨናነቁ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ለህክምና የሚያግዙ መድኃኒትና ግብአቶች ከታካሚዎች ቁጥር ጋር እንደማይመጣጠንም  ገልጸዋል።

ሁኔታው አስገዳጅ እየሆነ በመምጣቱ የህክምና ማእከላትን ለማስፋት ትምህርት ቤቶች፣የወጣት ማእከላትና አዳራሾች ለዚሁ ተግባር እንደሚውሉም ተናግረዋል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ  የተካሄደ ጥናት 33 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ወረርሽኙን የመከላከል ሥራዎችን እንደሚያከናውን አመልክቷል።

ይሁን እንጂ በዓለም የጤና ድርጅት የሚወጡ የመከላከል መመሪያዎችን በትክክል የሚተገብሩትን ለመለየት በተደረገው ጥናት ደግሞ ከግማሽ በታች የሚሆኑት ብቻ ስራውን በትክክል እንደሚያከናውኑ አሳይቷል ብለዋል።

በዚህም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም፣አካላዊ ርቀት መጠበቅና የእጅ ንጽህናን መጠበቅ ላይ ወጥነት እንደሚጎድልና ይህም  ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ወይዘሮ ሳህረላ ተናግረዋል።

አገሪቱ ካላት የህክምና ቁሳቁስና መድኃኒት አቅርቦት ጋር አለመመጣጠን ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ሕይወታቸው በቀላሉ ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የሕክምና ባለሙያው ዶክተር ይፍራሸዋ ዘውዴ ተናግረዋል።

ርቀትን መጠበቅ ዋነኛው የመከላከያ መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀምም ቢሆን በአብዛኛው መመሪያውን ተከትሎ ጥቅም ላይ እንደማይውል አመልክተዋል።

በተለይም መገናኛ ብዙኃን በህብረተሰቡ ውስጥ  የሚታየውን መዘናጋት ለመግታት  ተከታታይነት ያላቸው ተግባራት እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የጤና ባለሙያዎች፣ወጣቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በየቦታው በመዘዋወር ይሰጡት የነበረው የግንዛቤና የመከላከል ሥራ መቋረጥ መዘናጋት ከፈጠሩ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መዘናጋቱ በጨመረ ቁጥር ለሞት የመጋለጡ እድል የሚሰፋ ይሆናል ያሉት ዶክተር ይፍራሸዋ፣ ይህም ቫይረሱን በመቆጣጠር ረገድ ከአቅም በላይ ሆኖ ዋጋ ያስከፍላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ። 

በተጨማሪም አገሪቱ ከጤናው ጎን ለጎን በምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ላይ እንቅፋት እንደሚሆን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ ተይዘው በህክምና ላይ ያሉ 80 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ምንም ዓይነት ምልክት እንደማይታይባቸው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም