ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ የምርመራ ዘመቻ ተጀመረ

አሶሳ፤ ነሐሴ 06/2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል በቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎች የሚረዳ የምርመራ ዘመቻ ተጀመረ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አሻድሊ ሐሰን እንዳሉት በክልሉ  ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ እስከ ቀበሌ አደረጃጀት በመፍጠር የተጠናከረ መከላከል ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል። "ውጤትም ተገኝቶበታል "ብለዋል።

ባለፈው ሐምሌ ወር ግን መንግሥታዊ ተቋማትን ጨምሮ በበጎ ፈቃደኞችና በሌሎችም የኅብረተሰቡ ክፍሎች በታየ መዘናጋት የመከላከሉ ሥራ መቀዛቀዙን ገልጸው፤ በዚህም ምክንያት በክልሉ ባለፈው አንድ ወር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን አመላክተዋል።

እስካሁን በክልሉ 213 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በምርመራ መረጋገጡን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ 81 ሲያገግሙ ቀሪዎቹ በሕክምና ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 98 በመቶ ያህሉ ምንም የሕመም ምልክት እንዳልታየባቸውና ይህም ከመቼውም ጊዜ በላይ  ጥንቃቄ የሚደረግበት ወቅት እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች የሰጡትን መረጃ በመጥቀስ  ገልጸዋል።

በሽታው በክልሉ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ በመምጣቱ ይህን ለመከላከል እስከ ነሐሴ 15 የሚቆይ የምርመራ ዘመቻ መጀመሩን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

የዘመቻው ዓላማ የቫይረሱን ሥርጭት መጠን በመለየት በቀጣይ ለሚከናወኑ የትምህርትና መሰል የመከላከል ሥራዎች ዝግጅት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በዘመቻው ከአምስት ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ምርመራ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

በቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ከተሞች፣ የጤና ተቋማትና የወሰን አካባቢ እንቅስቃሴዎች  በዘመቻው ትኩረት የሚደረግባቸው ናቸው ብለዋል።

ኅብረተሰቡም ከመዘናጋት ወጥቶ በሽታው የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ ጥንቃቄውን እንዲያደርግም አቶ አሻድሊጥሪ አቅርበዋል።

ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ደመራ ሂርጳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  ከቫይረሱ የሚጠነቀቁ የመኖራቸውን ያህል የሚዘናጉ ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ መታዘባቸውን ተናግረዋል።

"የበሽታው ሥርጭት በመንግሥት ጥረት ብቻ አይገታም" ያሉት  አስተያየት ሰጪው በሽታውን ለመከላከል ወጥ የሆነ አቋም ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአሶሳ ርቀትን በሚገባ የማይጠብቁ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማይጠቀሙ እና ያገለገሉ ጭምብሎች  በየሜዳው እንደሚጣሉ መመልከቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ማዕረጉ ተስፋው ነው።

አቶ ሐሰን መሀመድ በበኩላቸው ከመዘናጋት በመውጣት ንጽሕናን ከመጠበቅ ጀምሮ ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት ባለመገኘትና የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የሚመለከተው የመንግሥት አካልም በሽታውን በመከላከል ላይ ግዴለሽነት የሚያሳዩትን ያለማቋረጥ ማስተማር እንደሚጠበቅበትም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም