በሰሜን ሸዋ የገጠር መንገድ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ

51

ደብረ ብርሃን ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንድ ሺህ 143 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ በመገንባትና የነበሩትን በመጠገን ለአገልግሎት ማብቃቱን የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ገለጸ።

የመንገድ አዲስ ግንባታና  ጥገናው የተከናወነው በዞኑ አስር ወረዳዎች ነው።

በመምሪያው የዲዛይን ኮንትራት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሞገስ ዜና ለኢዜአ እንደተናገሩት አዲስ ከተገነባው ውስጥ  87 ኪሎ ሜትር ከዚህ በፊት  የመንገድ ተደራሽ ባልሆነባቸው  የገጠር አካባቢዎች ነው።

በሞጃና ወደራ፣ ሞረትና ጅሩ፣ በግሼ፣ በጣርማበርና ሌሎች ወረዳዎች የተገነባው መንገዱ በጋ ከክረምት ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም የተገነባና በአገልግሎት ብዛት ለብልሽት የተዳረገ አንድ ሺህ 56 ኪሎ ሜትር ጥገና መካሄዱንም አስረድተዋል።

ለመንገዱ ስራ   96  ሚሊዮን 300 ሺህ  ብር ወጪ እንደተደረገበት አመልክተው፤ ይህም የአካባቢው ማህበረሰብ በጉልበት፣ በገንዘብና የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ  አስተዋጽኦ ማበርከቱን  አስታውቀዋል።

ቀበሌን ከቀበሌ እና ከዋና መንገድ በሚያገናኘው በዚህ የመንገድ ግንባታ ሂደት  ከአራት ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን   አቶ ሞገስ  ጠቅሰዋል።

በዞኑ ባለው አስቸጋሪ መልካዓ ምድራዊ  አቀማመጥ ችግር በህብረተሰብ ተሳትፎም ሆነ በወረዳ በጀት ከአቅም በላይ የሆኑ የክልሉን መንግስት ውሳኔ የሚሹ 481 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዳለም አመልክተዋል።

በባሶና ወራና ወረዳ የካሲማ ቀበሌ አርሶ አደር ጌታቸው ዳኜ በሰጡት አስተያየት የአካባቢው አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ መንገድ በቀላሉ እንዳይሰራ አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም የተሽከርካሪ አገልግሎት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ወላድ እናቶችና የግብርና ግብዓቶችን በቀላሉ ለማጓጓዝም ተቸግረው መቆየታቸውን ገልጸው፤ የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው የነበረው ከ"ዘንዶ ጉር ካስማ "የተገነባው መንገድ ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው ተናግረዋል።

አሁን የታመመን ሰው በተሽከርካሪ ወደ ህክምና ተቋም ማድረስ እንዲሁም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በቀላሉ አጓጉዘው መጠቀም እንደቻሉም ጠቅሰዋል።

የመንገዱን ደህንነት በመጠበቅና በመንከባከብ ዘላቂነት እንዲኖረው በግንባታው የጀመሩትን የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ በጥገናውም  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በአካባቢያቸው የተገነባው መንገድ የሚያመርቱትን አትክልትና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀላሉ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ  አርሶ አደር ማሙሽ ወርቁ ናቸው።

በሰሜን ሸዋ ዞን  በገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም እስካሁን አንድ ሺህ 426 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ከመንገድና ትራንስፖርት መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም