በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተፈጠረው ሰላም ደስታችን ወደር የለውም- ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተፈጠረው ሰላም ደስታችን ወደር የለውም- ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን
አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች ህዝብ አንድ ሆኖ ሳለ ለሁለት አስርት አመታት ያክል ተለያይቶ ዝምድናቸውም ተራርቆ ኖሯል። ይሁንና ሁለቱ አገራት ጦርነት ባወጁበት በ1990ዎቹ መጀመሪያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ብሎም ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ መቀጠላቸው በአገራቱ ሕዝቦች ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ ተጽእኖ ሲያደርስ ቆይቷል። በድንበር አካባቢም የመሠረተ ልማት ሥራዎች ያልተካሄዱበትና በድምሩ አከባቢው ላይ ልማት የራቀ መሆኑ ይገለጻል። በአገራቱ መካከል እርቅና ሰላም ይሰፍን ዘንድ ህዝቦቹም ለዘመናት ሲናፍቁት የኖሩትን በአብሮነትና በአንድነት የመኖር ህልም አሁን ላይ እውን እየሆነ ይመስላል። የኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላም ጉዳይ ለሁለቱ አገራትም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድና ለቀጣናው ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ጥቅሞች መረዳት አያዳግትም። የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ያላቸው ሊበጠስ የማይችል ዘመናትን ያስቆጠረው የአብሮነት ታሪክ፣ የጋራ ባህል፣ እሴት፣ ሃይማኖትና ቋንቋ አሁንም ድረስ ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸው ጎልቶ ይታያል። የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ጥብቅ የሆነ ትስስር ባላቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች መካከል ያለፈውን የጥላቻ ግምብ በመናድና ልዩነታችንን በማጥበብ ብሎም ውስብስብ የሆኑ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ አጀንዳዎችን በመፍታት ረገድ አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየተካሄዱ መሆናቸውም ይታያል። ይህንን የተስፋ ጉዞ የተመለከቱና የዚህ ታሪካዊ ክስተት አካል የሆኑ የሁለቱ አገራት ህዝቦችም ደስታቸው ወደር አጥቶ ፊታቸው በአንባ ረጥቦ እየተመለከትን እንገኛለን። እናት ከልጇ፣ አባትም ከልጁ፣ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቱ ተለያይቶ መኖር እንዴት ይቻላል? ህዝቦቹም "የሰላም ዋጋው ውድ ነው፤ ይሄ በህልም እንጂ በእውን አይመስልም፤ የናፈቅናቸውን ቤተሰቦቻችንን ለማግኘትና ለመቀላቀል ናፍቀናል" ይላሉ ህዝቦቹ በደስታ ስሜት ውስጥ እንባና ሳቅ በተሞላው አኳኋን። ኢዜአ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያንና ኑሮአቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ ኤርትራውያን "በተፈጠረው እርቀ ሰላም ደስታችን ወደር የለውም" ይላሉ። ወጣት ዮናስ ገብረሚካኤል (ኤርትራዊ)"እኛ በጣም ደስ ብሎናል ወንድምና እህት ሲገናኙ ፋሚሊ ከፋሚሊ ጋር ሲገናኝ እጅግ በጣም ደስ ይላል። በመገናኘታችን በጣም ደስ ብሎኛል እናቴንም አባቴንም አግኝቻቸው ነበር በጣም ደስ ብሎኛል።" ኤርትራዊው ወጣት ዮሴፍ ሃይለከልካይ በበኩሉ ለዶክተር አብይ አህመድ በጣም ላመሰግነው እፈልጋለው ትላንት ደውዬ ነበር እናቴ ጋር ማለት በቃ ለማመን ይከብዳል ይሄ ነገር ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ነበር ሲል ስሜቱን ገልጻል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኤርትራ ህዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉት አቀባበል ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍቅር፣ ክብርና፣ በአብሮነት ተሳስሮ የመኖር ፍላጎቱን ያሳየበት ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም የተጀመረው የሰላም ጉዞ ይበልጥ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የሁለቱን አገራት ቁርኝት ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል። ወጣት ሄኖክ ሌሊሳ "በተደረገው እርቅ በጣም ደስተኞች ነን ኤርትራዊ እህት ወንድሞቻችንና እናት አባቶቻችን በዚህ እርቅ ያልተደሰተ ህዝብ የለም”። ወጣት ሚሚ ዘሪሁን “እንደ ሌላ አገር የምትታይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ሆና ማየታችን በእድሜያችን አናውቀውም አሁን ግን በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል” በእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ላይ የሁለቱም አገራት ህዝቦች ሚናቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባም ነው የገለጹት። በተለይም በሁለቱ አገራት ላይ ሰላምን በመስበክና ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ የሃይማኖት አባቶች መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኤርትራን በጎበኙበት ወቅት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በዲፕሎማሲ፣ በትራንስፖርት፣ በድንበር ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድ እንዲሁም በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለሃያ ዓመታት የነበራቸውን "ሞት አልባ ጦርነት" ወደ ሰላም ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተከትሎ የተለያዩ አለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮች እንደነ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሮይተርስና ዋሺንግተን ፖስት ሰፊ ሽፋን እየሰጡት ይገኛሉ። ቀጣይ የሁለቱ አገራት ጉዞና እጣ ፈንታስ ምን ይሆን?