ቀጥታ፡

የቻይና ፓርላማ ሊቀመንበር ሊ ዛንሹ አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ግንቦት  1/2010 የቻይና ፓርላማ ሊቀመንበር ሊ ዛንሹ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ። የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሙፈሪያት ካሚል በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ሊቀመንበሩ የሚመሩት ልዑካን ቡድን ለሶስት ቀናት ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሚስተር ሊ ዛንሹ ከአፈ-ጉባኤዋ ጋር ባደረጉት ንግግር "ኢትዮጵያና ቻይና የቅርብ ወዳጅ አገሮች ናቸው" ብለዋል። አሁን ላይ የአገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ መሆኑን የገለጹት ሊ ዛንሹ፣ በነበራቸው ትስስርም በሁሉም ዘርፎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል። ወደፊትም ግንኙነታቸው ከዚህ በበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡ ሚስተር ሊ ዛንሹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ላይ እንደሚወያዩም ገልጸዋል። አቀባበል ላደረጉላቸው ለአዲሷ አፈ-ጉባኤ ለወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልም የእንኳን ደስ አለሽ ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤነት የተሾሙት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ኃላፊነቱን ከተረከቡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓርላማ ሊቀመንበር በመቀበላቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገለጸውላቸዋል። በቢሮአቸው በሚኖራቸው የሁለትዮሽ ውይይትም ከሊቀ-መንበር ሊ ዛንሹ ጋር ጥሩ የስራ ልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በቻይና ፓርላማ የሊቀ መንበር ኃላፊነት ከአገሪቷ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥሎ ሶስተኛው ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ መሆኑ ይነገራል። በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ኢትዮጵያና ቻይና ባለፈው ዓመት ግንኙነቱን ወደ ሁለገብ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማሳደጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም