ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2012 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ደን፣አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።
በኮሚሸኑ የደን ልማት ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ቢተው ሽባባው እንዳሉት በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የተተከሉ ችግኞችን ከሰደድ እሳትና ከእንስሳት ንኪኪ የመጠበቅ፣የማረም፣የመኮትኮትና ውሃ ማጠጣት ይሰራል።
ችግኞችን ከመትከል በዘለለ ጸድቀው ለአላማ አንዲውሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የችግኞችን ጽድቀት መጠን ለማስፋት ለተቋማት በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ መደረጉን የሚናግሩት አቶ ቢተው በስራቸውም ጠንካራ አፈጻጸም ላሳዩት ማበረታቻ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ የሚተክለው ችግኝ ከሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ለማስተካከል ጉልህ ድርሻ እንዳለው በመገንዘብ ለተከሏቸው ችግኞች ክብካቤ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በ2011 የተከላቸውን ችግኞች ሙሉ በሙሉ መጽደቁን የሚገልጹት ደግሞ የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኘነት ሃላፊ ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነህ ናቸው፡፡
ባለፈው አመት የተተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ በበጋ ወራት ውሃ በቦቲ በማመላለስ ማጠጣትና መኮትኮታቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ አያልሰው ተግባሩን በማስቀጠል በዘንድሮው አመት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው አመት በሁሉም ቅርንጫፎቹ 270ሺ ችግኞች መትከሉን የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው።
የባንኩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ የአብስራ ከበደ እንዳሉት በሰው ሃብት የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም በየጊዜው ውሃ የማጠጣት፣ የመኮትኮትና የማረም ስራዎች ከተከሏቸው ችግኞች 80 በመቶዎቹ ጸድቀዋል።
በዘንድሮው አመትም 1 ሚሊዮን ችግኞች መትከላቸውን የሚገልጹት አቶ የአብስራ ከባለፈው አመት በወሰዱት ልምድ በተሻለ መንገድ ለመንከባከብ ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡