የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለሌሎች አገራት ተሞክሮ እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለሌሎች አገራት ተሞክሮ እየሆነ ነው
አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለሌሎች አገራት በመልካም ተሞክሮነት እየተወሰደ መሆኑ ተነገረ።
የተባበሩትመንግስታቱ ድርጅት ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ያከናወነ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለመርሃ ግብሩ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።
የተቋማቱ አመራሮችና ሠራተኞች በአዲስ አበባ በተለምዶ ታቦት ማደሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 2 ሺህ 700 ሀገር በቀል ችግኞችን ተክለዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሯ አገር በቀል ችግኞችን ማካተቷ ተፈጥሮና አካባቢን ወደነበረበት መመለስን ዓላማ በማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።
የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ካለፉት ዓመታት የተከላ መርሃ-ግብሮች የተወሰደው ትምህርት በዚህ ዓመት ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት እንዲሰጥ ረድቷል ነው ያሉት።
የተፈጥሮ ሚዛኑን የጠበቀ አካባቢ ለትውልድ ለማስረከብ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የተባበሩትመንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ የደን ሽፋንን ወደነበረበት ከመመለስ በላይ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማሳካት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ዶክተር ካትሪንሕዝቡ ለራሱና ለመሬት ደህንነት ሲል ኮቪድ-19ን እየተከላከለና ህጻናትንም እያስተማረ ችግኝ ይትከል ብለዋል።
ኮሚሽነር ፍቃዱ በየነ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሌሎች አገራትም እየጀመሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችምተቋማት ተመሳሳይ ስራዎችን እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።